ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዳንኤል 7:16-27 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

16. በዚያ ከቆሙት ወደ አንዱ ቀርቤ፣ የዚህ ሁሉ እውነተኛ ትርጒም ምን እንደሆነ ጠየቅሁት።“እርሱም መለሰልኝ፤ የእነዚህንም ነገሮች ትርጒም እንዲህ ሲል ነገረኝ፤

17. ‘አራቱ ታላላቅ አራዊት ከምድር የሚነሡ መንግሥታት ናቸው፤

18. ነገር ግን የልዑሉ ቅዱሳን መንግሥቱን ይወስዳሉ፤ ለዘላለምም ይይዙታል፤ አዎን፤ ለዘላለም ይይዙታል።

19. “ከዚያም የሚያደቅቀውንና የሚበላውን፣ የቀረውንም ሁሉ በእግሮቹ የሚረጋግጠውን፣ የብረት ጥርሶችና የናስ ጥፍሮች የነበሩትን፣ ከሌሎቹ አራዊት የተለየና እጅግ አስፈሪ የሆነውን የአራተኛውን አውሬ እውነተኛ ትርጒም ማወቅ ፈለግሁ።

20. ደግሞም በራሱ ላይ ስላሉት ዐሥር ቀንዶች፣ ከመካከላቸው ብቅ ስላለው ቀንድና ከዚሁ ቀንድ ፊት ስለ ተነቃቀሉት ሦስት ቀንዶች፣ እንደዚሁም ከሌሎች ስለ በለጠው የሰው ዐይኖች የሚመስሉ ዐይኖች፣ በትዕቢትም የሚናገር አፍ ስለ ነበሩት ስለ ዚሁ ቀንድ ማወቅ ፈለግሁ።

21. እነሆም፤ ይህ ቀንድ በቅዱሳን ላይ ጦርነት ዐውጆ አሸነፋቸው፤

22. ይህም የሆነው ጥንታዌ ጥንቱ እስኪመጣና ለልዑሉ ቅዱሳን እስኪፈርድላቸው ድረስ ነበር፤ ከዚያም የልዑሉ ቅዱሳን መንግሥቱን የሚወርሱበት ዘመን መጣ።

23. “እርሱም እንዲህ አለኝ፣ ‘አራተኛው አውሬ በምድር ላይ የሚነሣ አራተኛው መንግሥት ነው። ከሌሎች መንግሥታት ሁሉ የተለየ ይሆናል፤ መላውንም ምድር እየረገጠና እያደቀቀ ይበላል።

24. ዐሥሩ ቀንዶች ከዚህ መንግሥት የሚወጡ ዐሥር ነገሥታት ናቸው፤ ከዚያም በኋላ ከእነርሱ የተለየ ሌላ ንጉሥ ይነሣል፤ ሦስቱንም ነገሥታት ያንበረክካል።

25. በልዑል ላይ የዐመፅ ቃል ይናገራል፤ የልዑልንም ቅዱሳን ያስጨንቃል፤ ለበዓላት የተመደበውን ጊዜና ሕግን ለመለወጥ ይሞክራል፤ ቅዱሳንም ለዘመን፣ ለዘመናት፣ ለዘመን እኩሌታም ለእርሱ ዐልፈው ይሰጣሉ።

26. “ነገር ግን የፍርድ ዙፋን ይዘረጋል፤ ሥልጣኑም ይወሰድበታል፤ ፈጽሞ ለዘላለም ይደመሰሳል።

27. ከዚያም ከሰማይ በታች ያሉ መንግሥታት ልዕልና፣ ሥልጣንና ታላቅነት ለልዑሉ ሕዝብ፣ ለቅዱሳን ይሰጣል። መንግሥቱ የዘላለም መንግሥት ይሆናል፤ ገዦች ሁሉ ያመልኩታል፤ ይታዘዙታልም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዳንኤል 7