ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዳንኤል 6:17-28 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

17. ድንጋይ አምጥተው በጒድጓዱ አፍ ላይ ገጠሙበት፤ ንጉሡም፣ በዳንኤል ላይ የተፈጸመው እንዳይለወጥ በራሱ የቀለበት ማኅተምና በመሳፍንቱ ቀለበቶች አተመበት።

18. ንጉሡም ወደ ቤተ መንግሥቱ ተመለሰ፤ በዚያም ሌሊት ምግብ ሳይበላ፣ የሚያዝናናውም ነገር ሳይቀርብለት ዐደረ፤ እንቅልፍም ከእርሱ ራቀ።

19. በማለዳም ገና ጎሕ ሲቀድ፤ ንጉሡ ተነሥቶ ወደ አንበሶቹ ጒድጓድ እየተጣደፈ ሄደ።

20. ወደ ጒድጓዱም ቀርቦ በሐዘን ድምፅ ዳንኤልን፣ “የሕያው አምላክ አገልጋይ ዳንኤል ሆይ፤ ሁል ጊዜ የምታመልከው አምላክህ ከአንበሶቹ ሊያድንህ ችሎአልን?” ብሎ ተጣራ።

21. ዳንኤልም እንዲህ ብሎ መለሰ፤ “ንጉሥ ሆይ፤ ለዘላለም ንገሥ፤

22. ንጉሥ ሆይ፤ በፊቱ ቅን ሆኜ ስለ ተገኘሁ፣ በአንተም ፊት በደል ስላልተገኘብኝ፣ አምላኬ መልአኩን ልኮ የአንበሶቹን አፍ ዘጋ፤ እነርሱም አልጐዱኝም።”

23. ንጉሡ እጅግ ተደስቶ፤ ዳንኤልን ከጒድጓዱ እንዲያወጡት አዘዘ። ዳንኤል በአምላኩ ታምኖ ነበርና ከጒድጓድ በወጣ ጊዜ፣ አንዳች ጉዳት አልተገኘበትም።

24. በንጉሡ ትእዛዝ፣ ዳንኤልን በሐሰት የከሰሱትን ሰዎች፣ ከሚስቶቻቸውና ከልጆቻቸው ጋር አምጥተው፣ በአንበሶቹ ጒድጓድ ውስጥ ጣሏቸው፤ ገና ወደ ጒድጓዱ መጨረሻ ሳይደርሱም፣ አንበሶቹ ቦጫጨቋቸው፤ ዐጥንቶቻቸውንም ሁሉ ሰባበሩ።

25. ከዚያ በኋላ ንጉሥ ዳርዮስ፣ በምድር ላይ ለሚኖሩ ሕዝቦች፣ መንግሥታትና ልዩ ልዩ ቋንቋ ለሚናገሩ ሰዎች ሁሉ እንዲህ የሚል መልእክት ጻፈ፤“ሰላም ይብዛላችሁ!

26. “በማንኛውም የመንግሥቴ ግዛት ሰው ሁሉ፣ የዳንኤልን አምላክ እንዲፈራና እንዲያከብር ይህን ዐዋጅ አውጥቻለሁ።“እርሱ ለዘላለም የሚኖር፣ሕያው አምላክ ነውና፣መንግሥቱ አይጠፋም፤ለግዛቱም መጨረሻ የለውም።

27. እርሱ ይታደጋል፤ ያድናልም፤በሰማይና በምድር፣ምልክቶችንና ድንቆችን ያደርጋል፤ዳንኤልን፣ከአንበሶች አፍ አድኖታል።”

28. ስለዚህ ዳንኤል በዳርዮስ ዘመነ መንግሥትና በፋርሳዊው በቂሮስ ዘመነ መንግሥት ሁሉ ኑሮው ተሳካለት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዳንኤል 6