ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዳንኤል 4:9-28 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

9. እኔም እንዲህ አልሁት፤ “የጠቢባን አለቃ ብልጣሶር ሆይ፤ የቅዱሳን አማልክት መንፈስ በአንተ ውስጥ እንዳለ ዐውቃለሁ፤ ምንም ዐይነት ምስጢር አያስቸግርህም፤ ያየሁት ሕልም እነሆ፤ ተርጒምልኝ።

10. በዐልጋዬ ላይ ተኝቼ ሳለሁ ያየሁት ራእይ ይህ ነው፦ እነሆ በፊቴ በምድር መካከል ቁመቱ እጅግ ረጅም የሆነ ዛፍ ቆሞ ተመለከትሁ።

11. ዛፉም እጅግ አደገ፤ ጠነከረም፤ ጫፉም ሰማይ ደረሰ፤ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስም ይታይ ነበር።

12. ቅጠሎቹ ያማሩ፣ ፍሬዎቹ የተንዠረገጉ ነበሩ፤ በላዩም ለሁሉ የሚሆን ምግብ ነበረበት። የምድር አራዊት ከጥላው በታች ያርፉ ነበር፤ በቅርንጫፎቹም ላይ የሰማይ ወፎች ይኖሩ ነበር፤ ፍጥረትም ሁሉ ከእርሱ ይመገብ ነበር።

13. “በዐልጋዬ ላይ ተኝቼ ሳለሁ ባየሁት ራእይ አንድ ቅዱስ መልእክተኛ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ።

14. እርሱም ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፤ ‘ዛፉን ቊረጡ፤ ቅርንጫፎቹን ጨፍጭፉ፤ ቅጠሎቹን አራግፉ፤ ፍሬውንም በትኑ፤ ከሥሩ ያሉት እንስሶች፣ በቅርንጫፎቹም ላይ ያሉት ወፎች ይሽሹ።

15. ነገር ግን ጒቶውና ሥሩ በሜዳው ሣር ላይ በብረትና በናስ ታስሮ በመሬት ውስጥ ይቈይ።“ ‘በሰማይ ጠል ይረስርስ፤ በጥሻም ውስጥ ከአራዊት ጋር ይኑር።

16. አእምሮው ከሰው አእምሮ ይለወጥ፤ የእንስሳም አእምሮ ይሰጠው፤ ሰባት ዓመትም ይለፍበት።

17. “ ‘ውሳኔው በመልእክተኞች ተገልጾአል፤ ፍርዱም በቅዱሳኑ ተነግሮአል፤ ይኸውም፣ ልዑል በሰዎች መንግሥታት ሁሉ ላይ እንደሚገዛና እነዚህንም መንግሥታት ለወደደው እንደሚሰጥ፣ ከሰዎችም የተናቁትን በላያቸው እንደሚሾም፣ ሕያዋን ሁሉ ያውቁ ዘንድ ነው።’

18. “እኔ ናቡከደነፆር ያየሁት ሕልም ይህ ነው፤ አሁንም ብልጣሶር ሆይ፤ በመንግሥቴ ካሉ ጠቢባን ሁሉ አንዳቸውም ሊተረጒሙልኝ ስላልቻሉ፣ ምን ማለት እንደሆነ ንገረኝ። አንተ የአማልክት መንፈስ በውስጥህ ስላለ ልትተረጒምልኝ ትችላለህ።

19. ከዚያም ብልጣሶር የተባለው ዳንኤል ለጥቂት ጊዜ በጣም ታወከ፤ ሐሳቡም አስደነገጠው። ንጉሡም፣ “ብልጣሶር ሆይ፤ ሕልሙም ሆነ ትርጒሙ አያስደንግጥህ” አለው።ብልጣሶርም እንዲህ ብሎ መለሰ፤ “ሕልሙ ለሚጠሉህ ይሁን፤ ትርጒሙም ለጠላቶችህ!

20. እጅግ አድጎና ጠንክሮ ያየኸው ዛፍ፣ ጫፉም እስከ ሰማይ ደርሶ በምድር ሁሉ የሚታየው፣

21. ቅጠሎቹ የሚያምሩ፣ ፍሬውም ተንዠርግጎ ለሁሉ ምግብ የሆነው፣ የዱር አራዊት መጠለያ የሆነውና በቅርንጫፎቹ ላይ ለሰማይ ወፎች ጎጆ መሥሪያ ያለው፣

22. ንጉሥ ሆይ፤ ያ ዛፍ አንተ ነህ፤ ታላቅና ብርቱ ሆንህ፤ ታላቅነትህ አድጎ እስከ ሰማይ ደረሰ፤ ግዛትህም እስከ ምድር ዳርቻ ተንሰራፋ።

23. “ንጉሥ ሆይ፤ አንተ፣ ‘ዛፉን ቊረጡ፣ አጥፉትም፤ በብረትና በናስ የታሰረውን ጒቶና ሥሩን በሜዳው ሣር ላይ በብረትና በናስ ታስሮ በመሬት ውስጥ ይቈይ፤ በሰማይ ጠል ይረስርስ፤ እንድ ዱር አራዊትም ይኑር፤ ሰባት ዓመትም ይለፍበት’ እያለ ከሰማይ የወረደውን ቅዱሱን መልእክተኛ አየህ።

24. “ንጉሥ ሆይ፤ ትርጒሙ ይህ ነው፤ ልዑሉ በንጉሡ በጌታዬ ላይ ያወጣው ዐዋጅ ይህ ነው፤

25. ከሕዝብ ተለይተህ ትሰደዳለህ፤ ዱር አራዊትም ጋር ትኖራለህ። እንደ ከብት ሣር ትበላለህ፤ በሰማይ ጠልም ትረሰርሳለህ፤ ልዑሉ በሰዎች መንግሥታት ሁሉ ላይ እንደሚገዛና እነዚህንም መንግሥታት ለወደደው እንደሚሰጥ እስክታውቅ ድረስ ሰባትዓመታት ያልፉብሃል።

26. የዛፉ ጒቶ ከነሥሩ እንዲቀር መታዘዙ፣ ሥልጣን ከሰማይ መሆኑን ስታውቅ መንግሥትህ እንደሚመለ ስልህ ያመለክታል።

27. ስለዚህ ንጉሥ ሆይ፤ ምክሬን ስማ፤ ኀጢአት መሥራትን ትተህ ትክክለኛ የሆነውን አድርግ፤ ክፋትን ትተህ ለተጨቈኑት ቸርነትን አድርግ፤ ምናልባት በሰላም የምትኖርበት ዘመን ይራዘምልህ ይሆናል።”

28. ይህ ሁሉ በንጉሡ በናቡከደነፆር ላይ ደረሰ፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዳንኤል 4