ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዳንኤል 4:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ከንጉሥ ናቡከደነፆር፣ በምድር ሁሉ ለሚኖሩ ሕዝቦች፣ መንግሥታትና ልዩ ልዩ ቋንቋዎችን ለሚናገሩ ሰዎች ሁሉ፤ ሰላም ይብዛላችሁ!

2. ልዑል አምላክ ያደረገልኝን ታምራዊ ምልክቶችንና ድንቅ ሥራዎች ስነግራችሁ እጅግ ደስ እያለኝ ነው።

3. ምልክቱ እንዴት ታላቅ ነው!ድንቁስ እንዴት ብርቱ ነው!መንግሥቱ የዘላለም መንግሥት ነው፤ግዛቱም ከትውልድ እስከ ትውልድ ይኖራል።

4. እኔ ናቡከደነፆር በቤቴ ደልቶኝ በቤተ መንግሥቴም ተመችቶኝ እኖር ነበር፤

5. አንድ ያስፈራኝ ሕልም አየሁ፤ በዐልጋዬ ላይ ተኝቼ ሳለሁ፣ ወደ አእምሮዬ የመጡት ምስሎችና ራእዮች አስደነገጡኝ።

6. ስለዚህ የባቢሎን ጠቢባን ሁሉ ወደ እኔ መጥተው ሕልሜን እንዲተረጒሙልኝ አዘዝሁ።

7. ጠንቋዮቹ፣ አስማተኞቹ፣ ኮከብ ቈጣሪዎቹና መተተኞቹ በመጡ ጊዜ ሕልሙን ነገርኋቸው፤ ነገር ግን ሊተረጒሙልኝ አልቻሉም።

8. በመጨረሻም በአምላኬ ስም ብልጣሶር ተብሎ የተጠራውና የቅዱሳን አማልክት መንፈስ ያለበት ዳንኤል ገብቶ በፊቴ ቆመ፤ ሕልሜንም ነገርሁት።

9. እኔም እንዲህ አልሁት፤ “የጠቢባን አለቃ ብልጣሶር ሆይ፤ የቅዱሳን አማልክት መንፈስ በአንተ ውስጥ እንዳለ ዐውቃለሁ፤ ምንም ዐይነት ምስጢር አያስቸግርህም፤ ያየሁት ሕልም እነሆ፤ ተርጒምልኝ።

10. በዐልጋዬ ላይ ተኝቼ ሳለሁ ያየሁት ራእይ ይህ ነው፦ እነሆ በፊቴ በምድር መካከል ቁመቱ እጅግ ረጅም የሆነ ዛፍ ቆሞ ተመለከትሁ።

11. ዛፉም እጅግ አደገ፤ ጠነከረም፤ ጫፉም ሰማይ ደረሰ፤ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስም ይታይ ነበር።

12. ቅጠሎቹ ያማሩ፣ ፍሬዎቹ የተንዠረገጉ ነበሩ፤ በላዩም ለሁሉ የሚሆን ምግብ ነበረበት። የምድር አራዊት ከጥላው በታች ያርፉ ነበር፤ በቅርንጫፎቹም ላይ የሰማይ ወፎች ይኖሩ ነበር፤ ፍጥረትም ሁሉ ከእርሱ ይመገብ ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዳንኤል 4