ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዳንኤል 3:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ንጉሡ ናቡከደነፆር ከፍታው ሥልሳ ክንድ፣ ወርዱ ስድስት ክንድ የሆነ የወርቅ ምስል አሠራ፤ በባቢሎንም አውራጃ በዱራ ሜዳ አቆመው።

2. ከዚያም መኳንንትን፣ ሹማምትን፣ አገረገዦችን፣ አማካሪዎችን፣ የግምጃ ቤት ኀላፊዎችን፣ ዳኞችን፣ ሌሎች የሕግ ዐዋቂዎችንና በየአውራጃው ያሉትን ሹማምንት ሁሉ ላቆመው ምስል ምረቃ በዓል እንዲመጡ ጠራ።

3. መኳንንቱ፣ ሹማምቱ፣ አገረገዦችን፣ አማካሪዎችን፣ የግምጃ ቤት ኀላፊዎቹ፣ ዳኞቹ፣ ሌሎች የሕግ ዐዋቂዎችና በየአውራጃው ያሉ ሹማምት ሁሉ ንጉሥ ናቡከደነፆር ላቆመው ምስል ምረቃ በዓል ተሰበሰቡ፤ በምስሉም ፊት ቆሙ።

4. ከዚያም ከፍ ባለ ድምፅ እንዲህ የሚል ዐዋጅ ታወጀ፤ “ሕዝቦች ሆይ፤ መንግሥታትና ልዩ ልዩ ቋንቋ የምትናገሩ ሰዎች ሁሉ፤ እንድታደርጉ የታዘዛችሁት ይህ ነው፦

5. የመለከትና የእንቢልታ፣ የመሰንቆና የክራር፣ የበገናና የዋሽንት እንዲሁም የዘፈን ሁሉ ድምፅ ስትሰሙ፣ ንጉሥ ናቡከደነፆር ላቆመው የወርቅ ምስል ተደፍታችሁ መስገድ አለባችሁ፤

6. ተደፍቶ የማይሰግድ ማንም ሰው ቢኖር፣ ወዲያውኑ በሚንበለበለው የእሳት እቶን ውስጥ ይጣላል።”

7. ስለዚህ የመለከትና የእንቢልታ፣ የመሰንቆና የክራር፣ የበገናና የዋሽንት፣ የዘፈንም ሁሉ ድምፅ በሰሙ ጊዜ ወዲያውኑ ሕዝቡ ሁሉ፣ መንግሥታትና ልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች፣ ንጉሥ ናቡከደነፆር ላቆመው የወርቅ ምስል ተደፍተው ሰገዱ።

8. በዚህ ጊዜ አንዳንድ ኮከብ ቈጣሪዎች ወደ ፊት ቀርበው አይሁድን ከሰሱ፤

9. ንጉሥ ናቡከደነፆርንም እንዲህ አሉት፤ “ንጉሥ ሆይ፤ ለዘላለም ንገሥ!

10. ንጉሥ ሆይ፤ አንተ እንዲህ ብለህ ዐዋጅ አውጥተህ ነበር፤ የመለከትና የእንቢልታ፣ የመሰንቆና የክራር፣ የበገናና የዋሽንት፣ የዘፈንም ድምፅ የሰማ ሁሉ ለወርቁ ምስል ተደፍቶ መስገድ አለበት፤

11. ማንም ተደፍቶ ለወርቁ ምስል ባይሰግድ በሚንበለበለው የእሳት እቶን ውስጥ ይጣላል።

12. ነገር ግን ንጉሥ ሆይ፤ በባቢሎን አውራጃ አስተዳዳሪዎች አድርገህ የሾምሃቸው ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ የሚባሉት አንዳንድ አይሁድ ትእዛዝህን አይቀበሉም፤ አማልክትህን አያገለግሉም፤ አንተም ላቆምኸው የወርቅ ምስል አይሰግዱም።”

13. ንጉሥ ናቡከደነፆር በታላቅ ቍጣ ሲድራቅን፣ ሚሳቅንና አብደናጎን አስጠራቸው፤ እነዚህንም ሰዎች በንጉሡ ፊት አቀረቧቸው፤

14. ናቡከደነፆርም እንዲህ አላቸው፤ “ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ ሆይ፤ እኔ ላቆምሁት ምስል አለመስገዳችሁ፣ አማልክቴንም አለማገልገላችሁ እውነት ነው?

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዳንኤል 3