ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዳንኤል 2:36-49 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

36. “ሕልሙ ይህ ነበር፤ አሁን ትርጒሙን ለንጉሥ እንናገራለን።

37. ንጉሥ ሆይ፤ አንተ የነገሥታት ንጉሥ ነህ፤ የሰማይ አምላክ መንግሥትንና ሥልጣንን፣ ኀይልንና ክብርን ሰጥቶሃል፤

38. የሰው ልጆችን፣ የምድር አራዊትንና የሰማይ ወፎችን በእጅህ አሳልፎ ሰጥቶሃል፤ በየትም ቦታ ቢሆኑ፣ በሁሉም ላይ ገዥ አድርጎሃል፤ እንግዲህ የወርቁ ራስ አንተ ነህ።

39. “ከአንተም በኋላ ከአንተ የሚያንስ ሌላ መንግሥት ይነሣል፤ ቀጥሎም በናስ የተመሰለው ሦስተኛ መንግሥት ይነሣል፤ መላውን ምድርም ይገዛል።

40. በመጨረሻም ሁሉን ነገር እንደሚቀጠቅጥና እንደሚሰብር ብረት ብርቱ የሆነ አራተኛ መንግሥት ይነሣል፤ ብረት ሁሉን ሰባብሮ እንደሚያደቅ ከእርሱ በፊት የነበሩትን መንግሥታት ሁሉ ሰባብሮ ያደቃቸዋል።

41. እግሮቹና ጣቶቹ ከፊል ብረትና ከፊል ሸክላ ሆነው እንዳየህ፣ እንዲሁ የተከፋፈለ መንግሥት ይሆናል፤ ነገር ግን ብረትና ሸክላ ተደባልቀው እንዳየህ በከፊል የብረት ጥንካሬ ይኖረዋል።

42. የእግሮቹ ጣቶች ከፊሉ ብረት ከፊሉ ሸክላ እንደሆኑ ሁሉ ይህም መንግሥት በከፊሉ ብርቱ በከፊሉ ደካማ ይሆናል።

43. ብረትና ሸክላ ተደባልቀው እንዳየህ ሁሉ ሕዝቡም ድብልቅ ይሆናል፤ ብረትና ሸክላ እንደማይዋሃድ ሁሉ ሕዝቡም በአንድነት አይኖሩም።

44. “በእነዚያ ነገሥታት ዘመን፣ የሰማይ አምላክ ፈጽሞ የማይፈርስና ለሌላም ሕዝብ የማይሰጥ መንግሥት ይመሠርታል፤ እነዚያን መንግሥታት ሁሉ ያደቃል፤ እስከ መጨረሻውም ያጠፋቸዋል፤ ይህ መንግሥት ራሱ ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።

45. የሰው እጅ ሳይነካው ከተራራ ተፈንቅሎ የወረደውና ብረቱን፣ ናሱን፣ ሸክላውን፣ ብሩንና ወርቁን ያደቀቀው ድንጋይ ራእይ ትርጓሜ ይህ ነው፦“ታላቁ አምላክ ወደ ፊት የሚሆነውን ለንጉሡ አሳይቶታል፤ ሕልሙ እውነት ነው፤ ትርጓሜውም የታመነ ነው።”

46. ከዚያም ንጉሥ ናቡከደነፆር በግንባሩ ተደፍቶ ለዳንኤል ሰገደለት፤ አከበረውም፤ መሥዋዕትና ዕጣንም እንዲያቀርቡለት አዘዘ።

47. ንጉሡም ዳንኤልን፣ “ይህን ምስጢር ልትገልጥ ችለሃልና፣ በእውነት አምላካችሁ የአማልክት አምላክና የነገሥታት ጌታ፣ ምስጢርንም ገላጭ ነው” አለው።

48. ንጉሡም ዳንኤልን በከፍተኛ ሥልጣን ላይ አስቀመጠው፤ እጅግ ብዙ ስጦታዎችንም ሰጠው፤ የመላው ባቢሎን አውራጃ ገዥ አደረገው፤ በባቢሎን ጠቢባን ሁሉ ላይም አለቃ አድርጎ ሾመው።

49. ከዚህም በላይ በዳንኤል አሳሳቢነት ንጉሡ ሲድራቅን፣ ሚሳቅንና አብደናጎን የባቢሎን አውራጃ አስተዳዳሪዎች አድርጎ ሾማቸው፤ ዳንኤል ግን በቤተ መንግሥት ተቀመጠ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዳንኤል 2