ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዳንኤል 2:1-15 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ናቡከደነፆር በነገሠ በሁለተኛው ዓመት ሕልም አለመ፤ መንፈሱ ታወከ፤ እንቅልፍም ከእርሱ ራቀ።

2. ያለመውንም ሕልም እንዲነግሩት ንጉሡ ጠንቋዮችን፣ አስማተኞችን፣ መተተኞችንና ኮከብ ቈጣሪዎችን እንዲጠሩ አዘዘ፤ እነርሱም ገብተው በፊቱ ቆሙ፤

3. እርሱም፣ “አንድ ሕልም አለምሁ፤ ሕልሙም ምን እንደሆነ ለማወቅ መንፈሴ ተጨንቆአል” አላቸው።

4. ከዚያም ኮከብ ቈጣሪዎቹ ለንጉሡ በአረማይክ ቋንቋ “ንጉሥ ሆይ፤ ለዘላለም ንገሥ! ሕልምህን ለአገልጋዮችህ ንገረን፤ እኛም እንፈታልሃለን” አሉት።

5. ንጉሡም ለኮከብ ቈጣሪዎቹ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ሕልሙንና ትርጒሙን ባትነግሩኝ አካላችሁ እንዲቈራረጥና ቤቶቻችሁም የፍርስራሽ ክምር እንዲሆኑ ወስኛለሁ

6. ነገር ግን ሕልሙንና ትርጒሙን ብትነግሩኝ፣ ስጦታና ሽልማት፣ ታላቅ ክብርም ከእኔ ትቀበላላችሁ፤ ሕልሙን ንገሩኝ፤ ትርጒሙንም አሳውቁኝ።”

7. እነርሱም እንደ ገና፣ “ንጉሥ ሕልሙን ለአገልጋዮቹ ይንገረን፤ እኛም እንተረጒመዋለን” ብለው መለሱ።

8. ንጉሡም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፤ “እኔ ምን ብዬ እንደ ወሰንሁ ስለምታውቁ፣ ጊዜ ለማራዘም እንደምትሞክሩ ተረድቼአለሁ፤

9. ሕልሙን ባትነግሩኝ፣ አንድ ቅጣት ይጠብቃችኋል፤ ሁኔታው ይለወጣል ብላችሁ በማሰብ የሚያሳስቱ ነገሮችንና ክፉ ሐሳቦችን ልትነግሩኝ አሲራችኋል፤ ስለዚህ ሕልሙን ንገሩኝ፤ ትርጒሙንም ልትነግሩኝ እንደምትችሉ በዚህ ዐውቃለሁ።”

10. ኮከብ ቈጣሪዎቹም ለንጉሡ እንዲህ ብለው መለሱ፤ “ንጉሡ የጠየቀውን ጥያቄ ሊመልስ የሚችል ሰው በምድር ላይ አይገኝም! ማንም ንጉሥ ምንም ያህል ታላቅና ኀያል ቢሆን፣ እንዲህ ዐይነት ነገር ማንኛውንም ጠንቋይ፣ አስማተኛ ወይም ኮከብ ቈጣሪን ጠይቆ ዐያውቅም።

11. ንጉሡ የሚጠይቀው እጅግ አስቸጋሪ ነገር ነው፤ በሰዎች መካከል ከማይኖሩት ከአማልክት በቀር ለንጉሡ የሚገልጽለት የለም።”

12. ይህም ንጉሡን እጅግ አበሳጨው፤ አስቈጣውም፤ በባቢሎን ያሉ ጠቢባን ሁሉ እንዲገደሉም አዘዘ፤

13. ጠቢባን ሁሉ እንዲገደሉም ዐዋጅ ወጣ፤ ዳንኤልንና ጓደኞቹን ፈልገው እንዲገድሉ ሰዎች ተላኩ።

14. የንጉሡ ዘበኞች አለቃ አርዮክ፣ የባቢሎንን ጠቢባን ለመግደል በመጣ ጊዜ፣ ዳንኤል በጥበብና በዘዴ አነጋገረው።

15. የንጉሡን መኰንን፣ “ንጉሡ እንዲህ ዐይነት ከባድ ዐዋጅ ያወጣው ስለ ምንድ ነው?” ሲል ጠየቀው፤ አርዮክም ነገሩን ለዳንኤል ገለጠለት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዳንኤል 2