ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዳንኤል 11:7-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

7. “ከዘመዶቿ አንዱ ስፍራዋን ሊይዝ ይነሣል፤ የሰሜንን ንጉሥ ሰራዊት ይወጋል፤ ምሽጎቹንም ጥሶ ይገባል፤ ከእነርሱም ጋር ተዋግቶ ድል ያደርጋል።

8. አማልክታቸውን፣ የብረት ምስሎቻቸውን፣ ከብርና ከወርቅ የተሠሩ የከበሩ ዕቃዎቻቸውን ይማርካል፤ ወደ ግብፅም ይወስዳል። ለጥቂት ዓመታትም ከሰሜኑ ንጉሥ ጋር ከመዋጋት ይቈጠባል።

9. የሰሜኑም ንጉሥ፣ የደቡቡን ንጉሥ ግዛት ይወራል፤ ነገር ግን አፈግፍጎ ወደ ገዛ አገሩ ይመለሳል።

10. ወንዶች ልጆቹም ለጦርነት ይዘጋጃሉ፤ እስከ ጠላት ምሽግ ደርሶ የሚዋጋና ሊቋቋሙት እንደማይቻል ጐርፍ የሚጠራርግ ታላቅ ሰራዊት ያሰባስባሉ።

11. “ከዚያም የደቡቡ ንጉሥ በቊጣ ወጥቶ የሰሜኑን ንጉሥ ይወጋል። የሰሜኑ ንጉሥ ታላቅ ሰራዊት ቢያሰባስብም ይሸነፋል።

12. የደቡቡ ንጉሥ ብዙ ሰራዊት በሚማርክበት ጊዜ ልቡ በትዕቢት ይሞላል፤ በብዙ ሺህ የሚቈጠሩ ሰዎችንም ይገድላል፤ ነገር ግን በድል አድራጊነቱ አይጸናም።

13. የሰሜን ንጉሥ ከመጀመሪያው የሚበልጥ ታላቅ ሰራዊት ያሰባስባል፤ ከብዙ ዓመትም በኋላ በትጥቅ እጅግ ከተደራጀ ታላቅ ሰራዊት ጋር ተመልሶ ይመጣል።

14. “በዚያም ዘመን ብዙዎች በደቡብ ንጉሥ ላይ ይነሣሉ፤ ራእዩ ይፈጸም ዘንድ፣ ከሕዝብህ መካከል ዐመፀኛ የሆኑ ሰዎች ይነሣሉ፤ ነገር ግን አይሳካላቸውም።

15. የሰሜኑም ንጉሥ መጥቶ የዐፈር ድልድል ይክባል፤ የተመሸገችውንም ከተማ ይይዛል። የደቡቡ ሰራዊትም ለመቋቋም ኀይል ያጣል፤ የተመረጡት ተዋጊዎቻቸው እንኳ ጸንተው መዋጋት አይችሉም።

16. ወራሪው ደስ ያሰኘውን ያደርጋል፤ ማንም ሊቋቋመው አይችልም። በመልካሚቱ ምድር ላይ ይገዛል፤ እርሷን ለማጥፋትም ኀይል ይኖረዋል።

17. በመንግሥቱ ያለውን ሰራዊት ሁሉ ይዞ ለመምጣት ይወስናል፤ ከደቡብም ንጉሥ ጋር ይስማማል፤ ይህንም መንግሥት ለመጣል ሴት ልጁን ይድርለታል፤ ይሁን እንጂ ዕቅዱ አይሳካለትም፤ ያሰበውም ነገር አይጠቅመውም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዳንኤል 11