ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዳንኤል 11:4-12 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. በኀይል እየገነነ ሳለም፣ መንግሥቱ ይፈርሳል፤ ወደ አራቱ የሰማይ ነፋሳትም ይከፋፈላል። መንግሥቱ ተወስዶ ለሌሎች ስለሚሰጥ፣ ለዘሩ አይተላለፍም፤ ኀይሉም እንደ መጀመሪያው አይሆንም።

5. “የደቡቡ ንጉሥ ይበረታል፤ ነገር ግን ከጦር አዛዦቹ አንዱ ከእርሱ የበለጠ የበረታ ይሆናል፤ ግዛቱም ታላቅ ይሆናል።

6. ከጥቂት ዓመታት በኋላም አንድነት ይፈጥራሉ። የደቡቡ ንጉሥ ሴት ልጅ ስምምነት ለማድረግ ወደ ሰሜኑ ንጉሥ ትሄዳለች፤ ነገር ግን ኀይሏን ይዛ መቈየት አትችልም፤ እርሱም ሆነ የእርሱ ኀይል አይጸናም። በእነዚያ ቀናት እርሷ ከቤተ መንግሥት አጃቢዎቿ፣ ከአባቷና ከደጋፊዎቿ ጋር ዐልፋ ትሰጣለች።

7. “ከዘመዶቿ አንዱ ስፍራዋን ሊይዝ ይነሣል፤ የሰሜንን ንጉሥ ሰራዊት ይወጋል፤ ምሽጎቹንም ጥሶ ይገባል፤ ከእነርሱም ጋር ተዋግቶ ድል ያደርጋል።

8. አማልክታቸውን፣ የብረት ምስሎቻቸውን፣ ከብርና ከወርቅ የተሠሩ የከበሩ ዕቃዎቻቸውን ይማርካል፤ ወደ ግብፅም ይወስዳል። ለጥቂት ዓመታትም ከሰሜኑ ንጉሥ ጋር ከመዋጋት ይቈጠባል።

9. የሰሜኑም ንጉሥ፣ የደቡቡን ንጉሥ ግዛት ይወራል፤ ነገር ግን አፈግፍጎ ወደ ገዛ አገሩ ይመለሳል።

10. ወንዶች ልጆቹም ለጦርነት ይዘጋጃሉ፤ እስከ ጠላት ምሽግ ደርሶ የሚዋጋና ሊቋቋሙት እንደማይቻል ጐርፍ የሚጠራርግ ታላቅ ሰራዊት ያሰባስባሉ።

11. “ከዚያም የደቡቡ ንጉሥ በቊጣ ወጥቶ የሰሜኑን ንጉሥ ይወጋል። የሰሜኑ ንጉሥ ታላቅ ሰራዊት ቢያሰባስብም ይሸነፋል።

12. የደቡቡ ንጉሥ ብዙ ሰራዊት በሚማርክበት ጊዜ ልቡ በትዕቢት ይሞላል፤ በብዙ ሺህ የሚቈጠሩ ሰዎችንም ይገድላል፤ ነገር ግን በድል አድራጊነቱ አይጸናም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዳንኤል 11