ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዳንኤል 1:6-18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. ከነዚህም መካከል ከይሁዳ የመጡት ዳንኤል፣ አናንያ፣ ሚሳኤልና አዛርያ ነበሩ፤

7. የጃንደረቦቹ አለቃም አዲስ ስም አወጣላቸው፤ ዳንኤልን ብልጣሶር፣ አናንያን ሲድራቅ፤ ሚሳኤልን ሚሳቅ፣ አዛርያን አብድናጎ ብሎ ጠራቸው።

8. ዳንኤል ግን በንጉሡ ምግብና የወይን ጠጅ እንዳይረክስ ወሰነ፤ በዚህ መንገድ ራሱን እንዳያረክስም የጃንደረቦቹን አለቃ ፈቃድ ጠየቀው።

9. እግዚአብሔርም ለዳንኤል በጃንደረቦቹ አለቃ ፊት ሞገስንና መወደድን ሰጠው።

10. ሆኖም የጃንደረቦቹ አለቃ ለዳንኤል፣ “መብሉንና መጠጡን የመደበላችሁን ጌታዬን ንጉሡን እፈራለሁ፤ በዕድሜ እንደ እናንተ ካሉ ወጣቶች ይልቅ ከስታችሁ ብትታዩ፣ በንጉሡ ዘንድ በራሴ ላይ አደጋ ታስከትሉብኛላችሁ።” ብሎ ነገረው።

11. ዳንኤልም የጃንደረቦቹን አለቃ በዳንኤል፣ በአናንያ፣ በሚሳኤልና በአዛርያስ ላይ የሾመውን መጋቢ እንዲህ አለው፤

12. “እባክህ አገልጋዮችህን ለዐሥር ቀን ያህል ፈትነን፤ ለመብል ከአትክልት፣ ለመጠጥም ከውሃ በስተቀር ምንም አይሰጠን፣

13. ከዚያም የእኛን መልክና የንጉሡን መብል የሚበሉትን ወጣቶች መልክ አስተያይ፤ በአገልጋዮችህ ላይ የወደድኸውን አድርግብን።”

14. እርሱም በዚህ ነገር ተስማማ፤ ለዐሥር ቀንም ፈተናቸው።

15. ከዐሥር ቀን በኋላም የንጉሡን መብል ከበሉት ከሌሎች ወጣቶች ይልቅ ጤናማዎችና ሰውነታቸው የወፈረ ሆነው ተገኙ።

16. ስለዚህ መጋቢው ምርጥ የሆነውን ምግባቸውንና ሊጠጡት የሚገባውን የወይን ጠጅ አስቀርቶ በምትኩ አትክልት ሰጣቸው።

17. እግዚአብሔር ለእነዚህ አራት ወጣቶች በማንኛውም ሥነ ጽሑፍና ትምህርት ዕውቀትንና ማስተዋልን ሰጣቸው፣ ዳንኤልም ማንኛውንም ራእይና ሕልም የመረዳት ችሎታ ነበረው።

18. ወደ እርሱ እንዲመጡ ንጉሡ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ፣ የጃንደረቦቹ አለቃ ወደ ናቡከደነፆር አቀረባቸው፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዳንኤል 1