ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 8:14-22 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

14. ኖኅ በመርከቡ ላይ ያለውን ክዳን አንሥቶ ተመለከተ፤ የመሬቱም ገጽ እንደ ደረቀ አየ። በሁለተኛው ወር፣ በሃያ ሰባተኛው ቀን ምድሪቱ ሙሉ በሙሉ ደረቀች።

15. ከዚያም እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ኖኅን እንዲህ አለው፤

16. “አንተና ሚስትህ፣ ልጆችህና የልጆችህ ሚስቶች ከመርከቧ ውጡ።

17. እንዲዋለዱ፣ እንዲራቡና በምድር ላይ እንዲበዙ፣ ከአንተ ጋር ያሉትን እንስሳትና በምድር ላይ የሚሳቡ ሕያዋን ፍጡራንን ሁሉ ይዘሃቸው ውጣ።”

18. ኖኅም ከልጆቹ፣ ከሚስቱና ከልጆቹ ሚስቶች ጋር ወጣ።

19. እንስሳቱ ሁሉ፣ ወፎችም፣ በምድር የሚንቀሳቀሱ ሁሉ በየወገናቸው ከመርከቧ ወጡ።

20. ከዚያም ኖኅ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መሠዊያ ሠራ፤ መሠዊያው ላይ ንጹሕ ከሆኑት እንስሳት ሁሉ፣ እንዲሁም ንጹሕ ከሆኑት ወፎች የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረበ፤

21. እግዚአብሔርም (ያህዌ) ደስ የሚያሰኘውን መዐዛ አሸተተ፤ በልቡም እንዲህ አለ፤ “ምንም እንኳ ሰው ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ሐሳቡ ወደ ክፋት ያዘነበለ ቢሆንም በእርሱ ምክንያት ሁለተኛ ምድርን አልረግማትም፤ አሁን እንዳደረግሁት ሕያዋን ፍጡራንን ዳግመኛ አላጠፋም።

22. “ምድር እስካለች ድረስ፣የዘር ወቅትና መከር፣ሙቀትና ቅዝቃዜበጋና ክረምት፣ቀንና ሌሊት፣አይቋረጡም።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 8