ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 50:14-25 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

14. ዮሴፍ አባቱን ከቀበረ በኋላ፣ ከወንድሞቹና ለአባቱ ቀብር አብረውት ሄደው ከነበሩት ሁሉ ጋር ወደ ግብፅ ተመለሰ።

15. የዮሴፍ ወንድሞች ከአባታቸው ሞት በኋላ፣ “ከፈጸምንበት በደል የተነሣ ዮሴፍ ቂም ይዞ ቢበቀለን ምን እናደርጋለን?” ተባባሉ።

16. ስለዚህ እንዲህ የሚል መልእክት ወደ ዮሴፍ ላኩ፤ “አባትህ ከመሞቱ በፊት እንዲህ የሚል ትእዛዝ አስተላልፎ ነበር፤

17. ‘ለዮሴፍ፣ “ወንድሞችህ በአንተ ላይ የፈጸሙትን ኀጢአትና ክፉ በደል ይቅር በላቸው” ብላችሁ ንገሩት።’ አሁንም፣ የእኛን የአባትህን አምላክ (ኤሎሂም) አገልጋዮች ኀጢአት ይቅር በለን።” መልእክታቸው ሲደርሰው ዮሴፍ አለቀሰ።

18. ከዚያም ወንድሞቹ መጡና በፊቱ ተደፍተው፣ “እኛ የአንተ ባሮች ነን” አሉት።

19. ዮሴፍ ግን እንዲህ አላቸው፤ “አትፍሩ፤ እኔን በእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ቦታ ማን አስቀመጠኝ?

20. እናንተ እኔን ለመጒዳት አስባችሁ አድርጋችሁት ነበር፤ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ግን ዛሬ እንደሚታየው ሁሉ የብዙዎችን ሕይወት ለማዳን ለበጎ ነገር አዋለው።

21. አሁንም ቢሆን አትፍሩ፤ ለእናንተና ለልጆቻችሁ የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ አደርግላችኋለሁ” በማለት አረጋግጦ፣ በደግ ቃል አናገራቸው።

22. ዮሴፍ ከአባቱ ቤተ ሰቦች ጋር በግብፅ ተቀመጠ፤ አንድ መቶ ዐሥር ዓመትም ኖረ፤

23. የኤፍሬምንም የልጅ ልጆች እስከ ሦስት ትውልድ ድረስ አየ። የምናሴ ልጅ ማኪር የወለዳቸውም ልጆች በዮሴፍ ጭን ላይ ተወለዱ።

24. ከዚህ በኋላ ዮሴፍ ወንድሞቹን፣ “እነሆ፤ የመሞቻዬ ጊዜ ተቃርቦአል፤ እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) በረድኤቱ ይጐበኛችሁና ከዚህ አገር ያወጣችኋል፤ ለአባቶቻችን ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ በመሐላ ተስፋ ወደ ሰጣቸው ምድር ያገባችኋል” አላቸው።

25. ዮሴፍም የእስራኤልን ልጆች፣ “እግዚአብሔር (ኤሎሂም) በረድኤቱ ያስባችኋል፤ በዚያን ጊዜ ዐፅሜን ከዚህ አገር ይዛችሁ እንድትወጡ” ሲል አስማላቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 50