ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 42:25-37 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

25. በስልቻዎቻቸው እህል እንዲሞሉላቸው፤ ብሩንም በያንዳንዱ ሰው ስልቻ ውስጥ መልሰው እንዲያስቀምጡና ለጒዞአቸው ስንቅ እንዲያሲዟቸው ዮሴፍ ትእዛዝ ሰጠ። ይህም ከተደረገላቸው በኋላ፣

26. እህላቸውን በአህዮቻቸው ጭነው ጒዞአቸውን ቀጠሉ።

27. በመንገድም ለዐዳር ሰፍረው ሳሉ፣ ከእነርሱ አንዱ ከያዘው እህል ላይ ለአህያው ለመስጠት ስልቻውን ሲፈታ፣ በስልቻው አፍ ላይ ብሩን አገኘ።

28. እርሱም ወንድሞቹን፣ “ኧረ ብሬ ተመልሶልኛል፤ ይኸው ስልቻዬ ውስጥ አገኘሁት” አላቸው።ሁሉም ልባቸው በድንጋጤ ተሞልቶ እየተንቀጠቀጡ በመተያየት፣ “እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ምን ሊያመጣብን ይሆን?” አሉ።

29. በከነዓን ምድር ወዳለው ወደ አባታቸው ወደ ያዕቆብ ከደረሱ በኋላ፣ ያጋጠማቸውን ሁሉ እንዲህ ብለው ነገሩት፤

30. “የአገሩ ጌታ የሆነው ሰው ምድሪቱን እንደምንሰልል ቈጥሮን በቍጣ ተናገረን።

31. እኛ ግን እንዲህ አልነው፤ ‘እኛ የታመንን ሰዎች እንጂ ሰላዮች አይደለንም።

32. እኛ የአንድ አባት ልጆች የሆን፣ ዐሥራ ሁለት ወንድማማቾች ነን፤ አንዱ የለም፤ ታናሽ ወንድማችን ግን ከአባታችን ጋር በከነዓን ይገኛል።’

33. “ከዚህ በኋላ የአገሩ ጌታ የሆነው ሰው እንዲህ አለን፤ ‘ታማኝ ሰዎች መሆናችሁን የማውቀው በዚህ ነው፤ ከእናንተ መካከል አንዱን ወንድማችሁን እዚህ እኔ ዘንድ ትታችሁ የተቀራችሁት ለተራቡት ቤተ ሰቦቻችሁ እህል ይዛችሁላቸው ሂዱ።

34. ነገር ግን ታናሽ ወንድማችሁን ወደ እኔ አምጡት። በዚያንም ጊዜ ታማኝ ሰዎች እንጂ ሰላዮች አለመሆናችሁን ዐውቃለሁ፤ ወንድማችሁንም መልሼ እሰጣችኋለሁ፤ እናንተም በምድሪቱ እንደ ልብ ለመዘዋወር ትችላላችሁ።” ’

35. እህሉንም ሲዘረግፉ በየስልቾቻቸው ውስጥ ብራቸው እንደ ተቋጠረ ተገኘ፤ የእያንዳንዳቸውን የተቋጠረ ብር ሲያዩም፣ እነርሱም ሆኑ አባታቸው ደነገጡ።

36. አባታቸው ያዕቆብም፣ “ያለ ልጅ እኮ አስቀራችሁኝ፤ ዮሴፍ የለም፤ ስምዖንም የለም፤ አሁን ደግሞ ብንያምን ልትወስዱ ትፈልጋላችሁ፤ ኧረ ምን ጒድ ነው የመጣብኝ!” አላቸው።

37. በዚህን ጊዜ ሮቤል አባቱን፣ “መልሼ ባላመጣው፣ ሁለቱን ወንዶች ልጆቼን ግደላቸው፤ ኀላፊነቱን ለእኔ ተውልኝ፤ እኔው መልሼ አመጣዋለሁ” አለው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 42