ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 42:14-25 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

14. ዮሴፍም እንዲህ አላቸው፤ “ነገርኋችሁ እኮ፤ ሰላዮች ናችሁ!

15. ታናሽ ወንድማችሁ እዚህ እስካልመጣ ድረስ ከዚህ ንቅንቅ እንደማትሉ በፈርዖን ስም እምላለሁ፤ ማንነታችሁ የሚረጋገጠውም በዚህ ነው።

16. በሉ፣ ከእናንተ አንዱን ላኩና ወንድማችሁን ይዞ ይመለስ፤ የቀራችሁት ግን የተናገራችሁት ቃል እስኪረጋገጥ ድረስ፣ እስር ቤት ትቈያላችሁ። እንደ ተናገራችሁት ካልሆነ ግን፣ በፈርዖን ስም እምላለሁ፤ ሁላችሁም ሰላዮች ናችሁ” አላቸው።

17. ሁሉንም ሦስት ቀን በእስር አቈያቸው።

18. በሦስተኛውም ቀን ዮሴፍ እንዲህ አላቸው፤ “እኔ እግዚአብሔርን (ኤሎሂም) ስለምፈራ እንዲህ በማድረግ ሕይወታችሁን አትርፉ።

19. ታማኝ ሰዎች ከሆናችሁ፣ ከመካከላችሁ አንዱ እዚህ እስር ቤት ሲቈይ፣ የቀራችሁት ግን ለተራቡት ቤተ ሰቦቻችሁ እህል ትወስዱላቸዋላችሁ፤

20. ታናሽ ወንድማችሁን ግን ይዛችሁ መምጣት አለባችሁ፤ በዚህም የተናገራችሁት ቃል እውነተኛነት ይረጋገጣል፤ እናንተም ከመሞት ትተርፋላችሁ።” እነርሱም ይህንኑ ለመፈጸም ተስማሙ።

21. እርስ በርሳቸውም፣ “ይኸው በወንድማችን ላይ ባደረስነው በደል ምክንያት ቅጣታችንን እየተቀበልን ነው። እርሱ እንደዚያ ተጨንቆ ስለ ሕይወቱ ሲማጠነን፣ እኛ አልሰማነውም ነበር፤ ይህ መከራ የደረሰብንም በዚሁ ምክንያት ነው” ተባባሉ።

22. ሮቤልም መልሶ፣ “በዚህ ልጅ ላይ፣ ‘ክፉ ነገር አታድርጉ’ ብዬ አልነበረምን? እናንተ ግን አልሰማችሁኝም፤ ስለዚህም ደሙ ከእጃችን ይፈለጋል” አላቸው።

23. ዮሴፍ የሚያነጋግራቸው በአስተርጓሚ ስለ ሆነ የሚነጋገሩትን እንደሚሰማቸው አላወቁም ነበር።

24. ከፊታቸውም ዘወር ብሎ አለቀሰ፤ ከዚያም ወደ እነርሱ ተመልሶ እንደ ገና አነጋገራቸው፤ ስምዖንንም ከእነርሱ ለይቶ ዐይናቸው እያየ አሰረው።

25. በስልቻዎቻቸው እህል እንዲሞሉላቸው፤ ብሩንም በያንዳንዱ ሰው ስልቻ ውስጥ መልሰው እንዲያስቀምጡና ለጒዞአቸው ስንቅ እንዲያሲዟቸው ዮሴፍ ትእዛዝ ሰጠ። ይህም ከተደረገላቸው በኋላ፣

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 42