ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 27:25-39 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

25. ከዚያም፣ “በል እንግዲህ ልጄ፤ እንድመርቅህ፣ አድነህ ካመጣኸው አቅርብልኝና ልብላ” አለው።ያዕቆብም ምግቡን ለአባቱ አቀረበለት፤ የወይን ጠጅም አመጣለት፤ እርሱም በላ፤ ጠጣም።

26. ከዚያም አባቱ ይስሐቅ፣ ያዕቆብን፣ “ልጄ ሆይ፤ እስቲ ቀረብ በልና ሳመኝ” አለው።

27. ያዕቆብም ቀርቦ ሳመው፤ ይስሐቅ የያዕቆብን ልብስ ካሸተተ በኋላ እንዲህ ብሎ መረቀው፤“እነሆ፤ የልጄ ጠረን፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንደ ባረከው፣እንደ መስክ መዐዛ ነው።

28. እግዚአብሔር (ኤሎሂም) የሰማይን ጠል፣የምድርንም በረከት፣የተትረፈረፈ እህልና የወይን ጠጅ ይስጥህ።

29. መንግሥታት ይገዙልህ፤ሕዝቦችም ተደፍተው እጅ ይንሡህ፤የወንድሞችህ ጌታ ሁን፤የእናትህም ልጆች ተደፍተው እጅ ይንሡህ፤የሚረግሙህ የተረገሙ ይሁኑ፤የሚባርኩህ የተባረኩ ይሁኑ።”

30. ይስሐቅ ያዕቆብን መርቆ እንዳበቃ፣ ያዕቆብ ገና ከአባቱ ዘንድ ሳይወጣ ወዲያውኑ፣ ወንድሙ ዔሳው ከዐደን ተመለሰ።

31. እርሱም ደግሞ ጣፋጭ ምግብ በማዘጋጀት ለአባቱ አቅርቦ፣ “አባቴ ሆይ፤ እንድትመርቀኝ፣ እስቲ ቀና በልና ካደንሁት ብላ” አለው።

32. አባቱ ይስሐቅም፣ “አንተ ደግሞ ማን ነህ?” ሲል ጠየቀው። እርሱም፣ “እኔማ የበኵር ልጅህ ዔሳው ነኝ” አለው።

33. በዚህ ጊዜ ይስሐቅ ክፉኛ እየተንቀጠቀጠ፣ “ታዲያ ቀደም ሲል አድኖ ያመጣልኝ ማን ነበር? አንተ ከመምጣትህ በፊት በልቼ መረቅሁት፤ እርሱም በእርግጥ የተባረከ ይሆናል” አለው።

34. ዔሳው የአባቱን ቃል ሲሰማ፣ ድምፁን ከፍ በማድረግ ምርር ብሎ አለቀሰ፤ አባቱንም፣ “አባቴ ሆይ፤ እኔንም ደግሞ እባክህ መርቀኝ” አለው።

35. ይስሐቅም፣ “ወንድምህ መጥቶ አታሎኝ ምርቃትህን ወስዶብሃል” አለው።

36. ዔሳውም፣ “ይህ ሰው ያዕቆብ መባሉ ትክክል አይደለምን? እኔን ሲያታልለኝ ይህ ሁለተኛ ጊዜው ነው፤ መጀመሪያ ብኵርናዬን ወሰደብኝ፤ አሁን ደግሞ ምርቃቴን ቀማኝ” አለ። ቀጥሎም፣ “ታዲያ ለእኔ ያስቀረኸው ምንም ምርቃት የለም?” ብሎ ጠየቀ።

37. ይስሐቅም ለዔሳው፣ “በአንተ ላይ የበላይነት እንዲኖረው፣ ወንድሞቹ ሁሉ አገልጋዮቹ እንዲሆኑ፣ እህሉ፣ የወይን ጠጁም የተትረፈረፈ እንዲሆንለት መርቄዋለሁ። ታዲያ ልጄ፣ ለአንተ ምን ላደርግልህ እችላለሁ?” ሲል መለሰለት።

38. ዔሳውም አባቱን፣ “አባቴ ሆይ፤ ምርቃትህ ይህችው ብቻ ናትን? እባክህ አባቴ፣ እኔንም መርቀኝ” አለው፤ ድምፁንም ከፍ አድርጎ አለቀሰ።

39. አባቱ ይስሐቅም እንዲህ ሲል መለሰለት፤“መኖሪያህከምድር በረከት፣ከላይም ከሰማይ ጠል የራቀ ይሆናል፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 27