ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 27:18-36 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

18. ያዕቆብም ወደ አባቱ ሄዶ፣ “አባቴ ሆይ፤ አለ፤ ይስሐቅም፣ “እነሆ፤ አለሁ ልጄ፤ ለመሆኑ አንተ ማን ነህ?” አለው።

19. ያዕቆብም አባቱን፣ “እኔ የበኵር ልጅህ ዔሳው ነኝ፤ ያዘዝኸኝን አድርጌአለሁ፤ እስቲ ቀና በልና እንድትመርቀኝ አድኜ ካመጣሁት ብላ” አለ።

20. ይስሐቅ ልጁን፣ “ልጄ ሆይ፤ ከመቼው ቀናህና መጣህ?” ሲል ጠየቀው። ያዕቆብም፣ “እግዚአብሔር አምላክህ (ያህዌ ኤሎሂም) አሳካልኝ” ብሎ መለሰለት።

21. ይስሐቅም ያዕቆብን፣ “ልጄ ሆይ፤ አንተ በእርግጥ ልጄ ዔሳው መሆንህን እንዳውቅ፣ እስቲ ቀረብ በልና ልዳብስህ” አለው።

22. ያዕቆብም ወደ አባቱ ወደ ይስሐቅ ተጠጋ፤ አባቱም በእጁ እየዳሰሰው፣ “ይህ ድምፅ የያዕቆብ ድምፅ ነው፤ እጆቹ ግን የዔሳው እጆች ናቸው” አለ።

23. እጆቹ እንደ ወንድሙ እንደ ዔሳው እጆች ጠጒራም ስለሆኑ፣ ይስሐቅ ያዕቆብን ለይቶ ማወቅ አልቻለም፤ ስለዚህ ባረከው።

24. ይስሐቅም፣ “በእርግጥ አንተ ልጄ ዔሳው ነህ?” ሲል ጠየቀው። ያዕቆብም፣ “አዎን፤ ነኝ” ብሎ መለሰ።

25. ከዚያም፣ “በል እንግዲህ ልጄ፤ እንድመርቅህ፣ አድነህ ካመጣኸው አቅርብልኝና ልብላ” አለው።ያዕቆብም ምግቡን ለአባቱ አቀረበለት፤ የወይን ጠጅም አመጣለት፤ እርሱም በላ፤ ጠጣም።

26. ከዚያም አባቱ ይስሐቅ፣ ያዕቆብን፣ “ልጄ ሆይ፤ እስቲ ቀረብ በልና ሳመኝ” አለው።

27. ያዕቆብም ቀርቦ ሳመው፤ ይስሐቅ የያዕቆብን ልብስ ካሸተተ በኋላ እንዲህ ብሎ መረቀው፤“እነሆ፤ የልጄ ጠረን፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንደ ባረከው፣እንደ መስክ መዐዛ ነው።

28. እግዚአብሔር (ኤሎሂም) የሰማይን ጠል፣የምድርንም በረከት፣የተትረፈረፈ እህልና የወይን ጠጅ ይስጥህ።

29. መንግሥታት ይገዙልህ፤ሕዝቦችም ተደፍተው እጅ ይንሡህ፤የወንድሞችህ ጌታ ሁን፤የእናትህም ልጆች ተደፍተው እጅ ይንሡህ፤የሚረግሙህ የተረገሙ ይሁኑ፤የሚባርኩህ የተባረኩ ይሁኑ።”

30. ይስሐቅ ያዕቆብን መርቆ እንዳበቃ፣ ያዕቆብ ገና ከአባቱ ዘንድ ሳይወጣ ወዲያውኑ፣ ወንድሙ ዔሳው ከዐደን ተመለሰ።

31. እርሱም ደግሞ ጣፋጭ ምግብ በማዘጋጀት ለአባቱ አቅርቦ፣ “አባቴ ሆይ፤ እንድትመርቀኝ፣ እስቲ ቀና በልና ካደንሁት ብላ” አለው።

32. አባቱ ይስሐቅም፣ “አንተ ደግሞ ማን ነህ?” ሲል ጠየቀው። እርሱም፣ “እኔማ የበኵር ልጅህ ዔሳው ነኝ” አለው።

33. በዚህ ጊዜ ይስሐቅ ክፉኛ እየተንቀጠቀጠ፣ “ታዲያ ቀደም ሲል አድኖ ያመጣልኝ ማን ነበር? አንተ ከመምጣትህ በፊት በልቼ መረቅሁት፤ እርሱም በእርግጥ የተባረከ ይሆናል” አለው።

34. ዔሳው የአባቱን ቃል ሲሰማ፣ ድምፁን ከፍ በማድረግ ምርር ብሎ አለቀሰ፤ አባቱንም፣ “አባቴ ሆይ፤ እኔንም ደግሞ እባክህ መርቀኝ” አለው።

35. ይስሐቅም፣ “ወንድምህ መጥቶ አታሎኝ ምርቃትህን ወስዶብሃል” አለው።

36. ዔሳውም፣ “ይህ ሰው ያዕቆብ መባሉ ትክክል አይደለምን? እኔን ሲያታልለኝ ይህ ሁለተኛ ጊዜው ነው፤ መጀመሪያ ብኵርናዬን ወሰደብኝ፤ አሁን ደግሞ ምርቃቴን ቀማኝ” አለ። ቀጥሎም፣ “ታዲያ ለእኔ ያስቀረኸው ምንም ምርቃት የለም?” ብሎ ጠየቀ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 27