ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 26:5-13 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

5. ይኸውም አብርሃም ቃሌን ሰምቶ፣ ድንጋጌዬን፣ ትእዛዜን፣ ሥርዐቴንና ሕጌን በመጠበቁ ነው።”

6. ስለዚህ ይስሐቅ በጌራራ ተቀመጠ።

7. የዚያም አገር ሰዎች ስለ ሚስቱ በጠየቁት ጊዜ፣ “እኅቴ ናት” አለ፤ ምክንያቱም፣ “ሚስቴ ናት ብል ርብቃ ቈንጆ ስለሆነች፣ ያገሬው ሰዎች በእርሷ ምክንያት ይገድሉኛል” በማለት ፈርቶ ነበር።

8. ይስሐቅ ብዙ ጊዜ በዚያ ከኖረ በኋላ፣ የፍልስጥኤም ንጉሥ አቢሜሌክ አንድ ቀን ወደ ውጭ ሲመለከት፣ ይስሐቅ ሚስቱን ርብቃን ሲዳራት አየ።

9. አቢሜሌክም ይስሐቅን ጠርቶ፣ “እርሷ ሚስትህ ሆና ሳለች፣ እንዴት እኅቴ ናት ትላለህ?” አለው።ይስሐቅም፣ “በእርሷ ሰበብ፣ ሕይወቴን እንዳላጣ ብዬ ነው” አለው።

10. አቢሜሌክም መልሶ፣ “እንዲህ ያለ ነገር ያደረግህብን ለምንድን ነው? ከሰዎቻችን አንዱ ሚስትህን ቢደፍራት ኖሮ በእኛ ላይ በደል አስከትለህብን ነበር እኮ!” አለው።

11. አቢሜሌክም፣ “ይህን ሰው ወይም ሚስቱን የነካ በሞት ይቀጣል” የሚል ትእዛዝ ለሕዝቡ ሁሉ አወጣ።

12. ይስሐቅም በዚያች ምድር ዘር ዘራ፣ እግዚአብሔርም (ያህዌ) ባረከለትና በዚያኑ ዓመት መቶ ዕጥፍ አመረተ።

13. ሰውየውም እጅግ ባለጠጋ እስኪሆን ድረስ ሀብት በሀብት ላይ እየተጨመረለት ሄደ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 26