ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 26:10-18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

10. አቢሜሌክም መልሶ፣ “እንዲህ ያለ ነገር ያደረግህብን ለምንድን ነው? ከሰዎቻችን አንዱ ሚስትህን ቢደፍራት ኖሮ በእኛ ላይ በደል አስከትለህብን ነበር እኮ!” አለው።

11. አቢሜሌክም፣ “ይህን ሰው ወይም ሚስቱን የነካ በሞት ይቀጣል” የሚል ትእዛዝ ለሕዝቡ ሁሉ አወጣ።

12. ይስሐቅም በዚያች ምድር ዘር ዘራ፣ እግዚአብሔርም (ያህዌ) ባረከለትና በዚያኑ ዓመት መቶ ዕጥፍ አመረተ።

13. ሰውየውም እጅግ ባለጠጋ እስኪሆን ድረስ ሀብት በሀብት ላይ እየተጨመረለት ሄደ።

14. ብዙ የበግና የፍየል መንጋ፣ ብዙ ከብት፣ ብዙ አገልጋዮችም ስለ ነበሩት፣ ፍልስጥኤማውያን ተመቀኙት።

15. ከዚህ የተነሣ ፍልስጥኤማውያን፣ አባቱ አብርሃም በሕይወት በነበረበት ጊዜ፣ የአብርሃም አገልጋዮች የቈፈሩአቸውን የውሃ ጒድጓዶች በሙሉ ዐፈር ሞልተው ደፈኑዋቸው።

16. አቢሜሌክም ይስሐቅን፣ “ከእኛ ይልቅ ኀያል ሆነሃልና አገራችንን ልቀቅልን” አለው።

17. ይስሐቅም ያን ቦታ ትቶ ሄደ፤ በጌራራ ሸለቆም ተቀመጠ።

18. ይስሐቅም በአባቱ በአብርሃም ጊዜ ተቈፍረው የነበሩትን፣ አባቱ ከሞተ በኋላ ፍልስጥኤማውያን የደፈኑአቸውን የውሃ ጒድጓዶች እንደ ገና እንዲከፈቱ አደረገ፤ አባቱ ቀድሞ ባወጣላቸው ስምም መልሶ ጠራቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 26