ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 23:1-13 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ሣራ አንድ መቶ ሃያ ሰባት ዓመት ኖረች፤

2. በከነዓን ምድር፣ በቂርያት አርባቅ ማለትም በኬብሮን ከተማ ሞተች፤ አብርሃምም ለሣራ ሊያለቅስና ሊያዝን መጣ።

3. ከዚያም አብርሃም ከተቀመጠበት ከሚስቱ ሬሳ አጠገብ ተነሣ፤ ኬጢያውያንንም እንዲህ አላቸው፤

4. “እኔ ለአገሩ እንግዳ፣ ለሰዉ ባዳ ሆኜ በመካከላችሁ የምኖር ነኝና ለመቃብር የምትሆን ቦታ ሽጡልኝ፤ የሚስቴንም ሬሳ ልቅበርበት።”

5. ኬጢያውያንም ለአብርሃም እንዲህ ሲሉ መለሱለት፤

6. “ስማን ጌታዬ፤ አንተ እኮ በእኛ ዘንድ እንደ ኀያል መስፍን ነህ፤ ከመቃብር ቦታችን በመረጥኸው ስፍራ ሬሳህን መቅበር ትችላለህ፤ ማናችንም ብንሆን የሞተብህን ሰው እንዳትቀብርበት የመቃብር ቦታችንን አንከለክልህም።”

7. ከዚያም አብርሃም ተነሥቶ የአገሬውን ሕዝብ፣ ኬጢያውያንን እጅ ነሣ፤

8. እንዲህም አላቸው፤ እንድቀብር ከፈቀዳችሁልኝ፣ አንዴ ስሙኝና የሰዓርን ልጅ ኤፍሮንን ስለ እኔ ሆናችሁ ለምኑልኝ።

9. ይኸውም በዕርሻው ድንበር ላይ ያለችውን መክፈላ የተባለችውን ዋሻውን እንዲሸጥልኝ ነው፤ በመካከላችሁም የመቃብር ቦታ እንድትሆነኝ በሙሉ ዋጋ እንዲሸጥልኝ ለምኑልኝ።

10. ኬጢያዊው ኤፍሮንም እዚያው መካከላቸው ተቀምጦ ስለ ነበር፣ ወደ ከተማው በር መግቢያ መጥተው የተሰበሰቡት ኬጢውያን በሙሉ እየሰሙ ለአብርሃም እንዲህ ሲል መለሰለት፤

11. “እንዲህ አይደለም ጌታዬ፤ አድምጠኝ፤ ዕርሻውን በውስጡ ካለው ዋሻ ጋር ውሰደው፤ እነሆ፤ በወገኖቼ ኬጢያውያን ፊት ሰጥቼሃለሁ፤ ሬሳህን ቅበርበት።”

12. አብርሃም እንደ ገና የአገሬውን ሕዝብ እጅ ነሣና

13. ሁሉም እየሰሙት፣ የዕርሻውን ቦታ ዋጋ ልክፈል፤ እባክህን ተቀበለኝና ሬሳዬን ልቅበርበት” አለው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 23