ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 21:3-14 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

3. አብርሃም፣ ሣራ የወለደችለትን ልጅ ስሙን ይስሐቅ አለው።

4. አብርሃም፣ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ባዘዘው መሠረት ልጁን ይስሐቅን በተወለደ በስምንተኛው ቀን ገረዘው።

5. አብርሃም፣ ልጁ ይስሐቅ ሲወለድለት፣ ዕድሜው መቶ ዓመት ነበረ።

6. ሣራም፣ “እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ሣቅ አድሎኛል፤ ስለዚህ፣ ይህን የሚሰማ ሁሉ ከእኔ ጋር ይሥቃል” አለች።

7. ደግሞም፣ “ለመሆኑ፣ ‘ሣራ ልጆች ታጠባለች’ ብሎ ለአብርሃም ማን ተናግሮት ያውቅ ነበር? ይኸው በስተርጅናው ወንድ ልጅ ወለድሁለት” አለች።

8. ሕፃኑ አደገ፤ ጡት መጥባቱንም ተወ። አብርሃምም ይስሐቅ ጡት በጣለባት ዕለት ታላቅ ድግስ ደገሰ።

9. በሌላ በኩል ደግሞ፣ ግብፃዊቷ አጋር ለአብርሃም የወለደችለት እስማኤል፣ በይስሐቅ ሲያሾፍበት ሣራ አየች፤

10. አብርሃምንም፣ “ይህችን ባሪያ ከነልጇ አባርልኝ፤ ምንም ቢሆን የዚህች ባሪያ ልጅ፣ ከልጄ ከይስሐቅ ጋር ውርስ አይካፈልም አለች።”

11. እስማኤል ልጁ ስለ ሆነ ነገሩ አብርሃምን እጅግ አስጨነቀው።

12. እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) አብርሃምን እንዲህ አለው፤ “ስለ ልጁም ሆነ ስለ አገልጋይህ አሳብ አይግባህ፤ ዘር የሚጠራልህ በይስሐቅ በኩል ስለ ሆነ፣ ሣራ የምትልህን ሁሉ ስማ።

13. የአገልጋይህም ልጅ የራስህ ልጅ ስለ ሆነ፣ እርሱንም ታላቅ ሕዝብ አደርገዋለሁ።”

14. በማግስቱ አብርሃም ማልዶ ተነሣ። ጥቂት ምግብ ወስዶ፣ ውሃ በእርኮት አድርጎ ለአጋር ሰጣት፤ በትከሻዋም አሸክሞአት ከነልጇ አሰናበታት። እርሷም ሄደች፤ በቤርሳቤህም ምድረ በዳ ትንከራተት ጀመር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 21