ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 21:17-28 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

17. እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) የልጁን ጩኸት ሰማ። የእግዚአብሔር (ኤሎሂም) መልአክ ከሰማይ አጋርን እንዲህ አላት፤ “አጋር ሆይ፤ ምን ሆነሻል? ልጅሽ ከተኛበት ሲያለቅስ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ሰምቶታል፤ ስለዚህ አትፍሪ።

18. ተነሥተሽ ልጁን አንሺው፤ ያዢውም፤ ታላቅ ሕዝብ አደርገዋለሁና።”

19. እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) ዐይኖቿን ከፈተላት፤ የውሃ ጒድጓድም አየች፤ ሄዳም በእርኮቱ ውሃ ሞልታ ልጇን አጠጣች።

20. እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ከልጁ ጋር ነበር፤ ልጁም እያደገ ሄደ፤ መኖሪያውንም በምድረ በዳ ውስጥ አደረገ፤ ጐበዝ ቀስተኛም ሆነ።

21. በፋራን ምድረ በዳ ሳለም፣ እናቱ ከግብፅ አንዲት ሴት አምጥታ አጋባችው።

22. በዚያን ጊዜ አቢሜሊክ ከሰራዊቱ አለቃ ከፊኮል ጋር ሆኖ አብርሃምን እንዲህ አለው፤ “በምታደርገው ነገር ሁሉ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ከአንተ ጋር ነው።

23. እንግዲህ እኔንና ልጆቼን፣ ዘሬንም በመሸንገል አንዳች ክፉ ነገር እንዳታደርስብን በእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ፊት ማልልኝ። እኔ ለአንተ ቸርነት እንዳደረግሁ፣ አንተም ለእኔና በእንግድነት ለተቀመጥህባት ለዚች ምድር ቸርነት አድርግ።”

24. አብርሃምም፣ “እሺ፤ እምላለሁ” አለ።

25. ከዚያም አብርሃም፣ የአቢሜሌክ አገልጋዮቹ ነጥቀው ስለያዙበት የውሃ ጒድጓድ መከፋቱን ለአቢሜሌክ ገለጠለት።

26. አቢሜሌክም፣ “መቼም ይህን ድርጊት ማን እንደ ፈጸመ በበኩሌ አላውቅም፤ አንተም አልነገርኸኝም፤ ነገሩንም ገና አሁን መስማቴ ነው” አለው።

27. ስለዚህ አብርሃም፣ በጎችና ከብቶች አምጥቶ ለአቢሜሌክ ሰጠው፤ ሁለቱም በመካከላቸው የስምምነት ውል አደረጉ።

28. አብርሃም ከመንጋው ሰባት እንስት በጎች ለየ፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 21