ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 19:1-16 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ሁለቱ መላእክት ምሽት ላይ ሰዶም ደረሱ፤ ሎጥም በሰዶም ከተማ መግቢያ በር ተቀምጦ ነበር፤ ሎጥም መላእክቱን ሲያይ ሊቀበላቸው ብድግ አለ፤ በግምባሩም ወደ ምድር ተደፍቶ እጅ ነሣቸው።

2. እርሱም፣ “ጌቶቼ፤ እባካችሁ ወደ እኔ ወደ ባሪያችሁ ቤት ጎራ በሉ፤ ከዚያም እግራችሁን ታጠቡ፤ አድራችሁም ጧት በማለዳ ጒዞአችሁን ትቀጥላላችሁ” አላቸው።እነርሱም፣ “አይሆንም፤ እዚሁ አደባባይ ላይ እናድራለን” አሉት።

3. ሎጥ ግን አጥብቆ ስለ ለመናቸው አብረውት ወደ ቤቱ ገቡ፤ ከዚያም ቂጣ ጋግሮ አቀረበላቸውና በሉ።

4. ከመተኛታቸውም በፊት፣ የሰዶም ከተማ ነዋሪዎች የሆኑ ወንድ ወጣቶችና ሽማግሌዎች ከያካባቢው መጥተው ቤቱን ከበቡት።

5. ሎጥንም ጠርተው፣ “በዚህች ምሽት ወደ ቤትህ የገቡት ሰዎች የት አሉ? ሩካቤ ሥጋ እንድንፈጽምባቸው ወደ ውጭ አውጣልን” አሉት።

6. ሎጥም ሊያነጋግራቸው ወደ ውጭ ወጣ፤ መዝጊያውን ከበስተ ኋላው ዘግቶ፣

7. እንዲህ አለ፤ “ወዳጆቼ ሆይ፤ እባካችሁ እንዲህ ያለውን ክፉ ነገር አታድርጉ።

8. እነሆ፤ ወንድ የማያውቁ ሁለት ሴቶች ልጆች አሉኝ። እነርሱን ላውጣላችሁና የፈለጋችሁትን አድርጉባቸው። በእነዚህ ሰዎች ላይ ግን አንዳች ነገር አታድርጉባቸው፤ እኔን ብለው ወደ ቤቴ ገብተዋልና።”

9. እነርሱም፣ “ዞር በል! ይህ ሰው ራሱ ትናንት ተሰዶ የመጣ ነው፤ ዛሬ ደግሞ ዳኛ ልሁን ይላል። ዋ! በእነርሱ ካሰብነው የከፋ እንዳና ደርስብህ!” አሉት፤ ከዚያም ሎጥን እየገፈታተሩ የበሩን መዝጊያ ለመስበር ተንደረደሩ።

10. ከቤቱ ውስጥ የነበሩት እንግዶች ግን እጃቸውን በመዘርጋት ስበው ወደ ውስጥ አስገቡት፤ በሩንም ዘጉ።

11. ከዚያም በሩን እንዳያገኙት በቤቱ ደጃፍ ላይ የተሰበሰቡትን ወጣቶችና ሽማግሌዎች ዐይን አሳወሩ።

12. ሁለቱ ሰዎችም ሎጥን እንዲህ አሉት፤ “በከተማዋ ውስጥ የሚኖሩ የአንተ የሆኑ ሰዎች አሉህ? ዐማቾች፣ ወንዶችና ሴቶች ወይም ሌሎች ዘመዶች ካሉህ ቶሎ ብለህ ከዚህ እንዲወጡ አድርግ፤

13. ይህን ስፍራ ልናጠፋው ነው። በሕዝቦቿ ላይ ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) የቀረበው ጩኸት ታላቅ በመሆኑ፣ እንድናጠፋት እግዚአብሔር ልኮናል።”

14. ሎጥ ከቤቱ ወጥቶ የሴት ልጆቹ እጮኞች የሆኑትን ዐማቾቹን፣ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ይህችን ከተማ ሊያጠፋት ነውና በፍጥነት ከዚህ ስፍራ ውጡ” አላቸው፤ ዐማቾቹ ግን የሚቀልድ መሰላቸው።

15. ሲነጋጋም መላእክቱ ሎጥን፣ “ከከተማዪቱ ጋር አብራችሁ እንዳትጠፉ፣ ሚስትህንና ሁለቱን ሴት ልጆችህን ይዘህ ከዚህ ቦታ በፍጥነት ውጣ” ብለው አቻኰሉት።

16. ሎጥ ሲያመነታም፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) ስለ ራራላቸው ሰዎቹ የእርሱን፣ የሚስቱንና የሁለት ሴቶች ልጆቹን እጅ ይዘው ከከተማዪቱ በደኅና አወጧቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 19