ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 19:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ሁለቱ መላእክት ምሽት ላይ ሰዶም ደረሱ፤ ሎጥም በሰዶም ከተማ መግቢያ በር ተቀምጦ ነበር፤ ሎጥም መላእክቱን ሲያይ ሊቀበላቸው ብድግ አለ፤ በግምባሩም ወደ ምድር ተደፍቶ እጅ ነሣቸው።

2. እርሱም፣ “ጌቶቼ፤ እባካችሁ ወደ እኔ ወደ ባሪያችሁ ቤት ጎራ በሉ፤ ከዚያም እግራችሁን ታጠቡ፤ አድራችሁም ጧት በማለዳ ጒዞአችሁን ትቀጥላላችሁ” አላቸው።እነርሱም፣ “አይሆንም፤ እዚሁ አደባባይ ላይ እናድራለን” አሉት።

3. ሎጥ ግን አጥብቆ ስለ ለመናቸው አብረውት ወደ ቤቱ ገቡ፤ ከዚያም ቂጣ ጋግሮ አቀረበላቸውና በሉ።

4. ከመተኛታቸውም በፊት፣ የሰዶም ከተማ ነዋሪዎች የሆኑ ወንድ ወጣቶችና ሽማግሌዎች ከያካባቢው መጥተው ቤቱን ከበቡት።

5. ሎጥንም ጠርተው፣ “በዚህች ምሽት ወደ ቤትህ የገቡት ሰዎች የት አሉ? ሩካቤ ሥጋ እንድንፈጽምባቸው ወደ ውጭ አውጣልን” አሉት።

6. ሎጥም ሊያነጋግራቸው ወደ ውጭ ወጣ፤ መዝጊያውን ከበስተ ኋላው ዘግቶ፣

7. እንዲህ አለ፤ “ወዳጆቼ ሆይ፤ እባካችሁ እንዲህ ያለውን ክፉ ነገር አታድርጉ።

8. እነሆ፤ ወንድ የማያውቁ ሁለት ሴቶች ልጆች አሉኝ። እነርሱን ላውጣላችሁና የፈለጋችሁትን አድርጉባቸው። በእነዚህ ሰዎች ላይ ግን አንዳች ነገር አታድርጉባቸው፤ እኔን ብለው ወደ ቤቴ ገብተዋልና።”

9. እነርሱም፣ “ዞር በል! ይህ ሰው ራሱ ትናንት ተሰዶ የመጣ ነው፤ ዛሬ ደግሞ ዳኛ ልሁን ይላል። ዋ! በእነርሱ ካሰብነው የከፋ እንዳና ደርስብህ!” አሉት፤ ከዚያም ሎጥን እየገፈታተሩ የበሩን መዝጊያ ለመስበር ተንደረደሩ።

10. ከቤቱ ውስጥ የነበሩት እንግዶች ግን እጃቸውን በመዘርጋት ስበው ወደ ውስጥ አስገቡት፤ በሩንም ዘጉ።

11. ከዚያም በሩን እንዳያገኙት በቤቱ ደጃፍ ላይ የተሰበሰቡትን ወጣቶችና ሽማግሌዎች ዐይን አሳወሩ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 19