ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 18:18-33 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

18. አብርሃም በእውነት ታላቅና ብርቱ ሕዝብ ይሆናል፤ የምድር ሕዝቦችም ሁሉ በእርሱ ይባረካሉ።

19. ትክክለኛና ቀና የሆነውን በማድረግ የእግዚአብሔርን (ያህዌ) መንገድ ይጠብቁ ዘንድ ልጆቹንና ከእርሱ በኋላ ቤተ ሰቦቹን እንዲያዝ መርጬዋለሁ፤ ይኸውም እግዚአብሔር (ያህዌ) ለአብርሃም የሰጠው ተስፋ ሁሉ እንዲፈጸም ነው።”

20. ደግሞም እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዲህ አለ፤ “በሰዶምና በገሞራ ላይ የሚሰማው ጩኸት እጅግ በዝቶአል፤ ኀጢአታቸውም እጅግ ከፍቶአል፤

21. አድራጎታቸው እኔ ዘንድ እንደ ደረሰው ጩኸት መሆኑን ለማየት ወደዚያው እወርዳለሁ፤ እንደዚያ ካልሆነም ዐውቃለሁ።”

22. ሰዎቹም ፊታቸውን ወደ ሰዶም አቅንተው ሄዱ፤ አብርሃም ግን በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት እንደ ቆመ ነበር።

23. አብርሃምም ወደ እርሱ ቀረብ ብሎ እንዲህ አለ፤ “በእርግጥ ጻድቁን ከኀጢአተኛው ጋር አብረህ ታጠፋለህን?

24. አምሳ ጻድቃን በከተማዪቱ ቢገኙ፣ በውኑ ነዋሪዎቹን ሁሉ ታጠፋለህን? በውስጧ ለሚገኙ አምሳ ጻድቃን ስትል ከተማዪቱን አትምርምን?

25. እንዲህስ አይሁን፤ ጻድቁን ከኀጢአተኛው ጋር እንዴት ትገድለዋለህ? ይህን የመሰለው አድራጎት ከአንተ ይራቅ፤ የምድር ሁሉ ዳኛ በቅን አይፈርድምን?”

26. እግዚአብሔርም (ያህዌ)፣ “በሰዶም ከተማ አምሳ ጻድቃን ባገኝ ለእነርሱ ስል አገሪቱን በሞላ እምራለሁ” አለ።

27. ደግሞም አብርሃም እንዲህ አለ፤ “እኔ ከንቱ፣ ትቢያና ዐመድ ሆኜ ሳለሁ ከጌታ (አዶናይ) ጋር ለመናገር አንዴ ደፍሬአለሁ፤

28. ለመሆኑ ከአምሳው ጻድቃን አምስት ቢጐድሉ በአምስቱ ሰዎች ምክንያት መላ ከተማዋን ታጠፋለህን?”እርሱም፣ “አርባ አምስት ጻድቃን ባገኝ አላጠፋትም” አለ።

29. አብርሃምም እንደ ገና፣ “ምናልባት አርባ ጻድቃን ቢገኙስ?” አለ እርሱም፣ “ለአርባው ስል እምራታለሁ” አለ።

30. ደግሞም አብርሃም፣ “ጌታዬ (አዶናይ) አይቈጣ፤ እባክህ ልናገር፤ ሠላሳ ጻድቃን ብቻ ቢገኙስ?”እርሱም፣ “ሠላሳ ባገኝ አላጠፋትም” ብሎ መለሰ።

31. አብርሃምም፣ “ከጌታ (አዶናይ) ጋር እናገር ዘንድ መቼም አንዴ ደፍሬአለሁና ምናልባት ሃያ ብቻ ቢገኙስ?” አለ።እርሱም፣ “ሃያ ቢገኙ፣ ለእነርሱ ስል እምራታለሁ” አለ።

32. አብርሃምም፣ “ጌታዬ (አዶናይ) አይቈጣ፤ አንድ ጊዜ ብቻ ልናገር፤ ምናልባት ዐሥር ብቻ ቢገኙስ?” አለ።እርሱም “ስለ ዐሥሩ ስል አላጠፋትም” ብሎ መለሰ።

33. እግዚአብሔር (ያህዌ) ከአብርሃም ጋር ንግግሩን ከጨረሰ በኋላ ሄደ፤ አብርሃምም ወደ ቤቱ ተመለሰ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 18