ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 17:6-15 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. ዘርህን እጅግ አበዛለሁ፤ ብዙ ሕዝብም አደርግሃለሁ፤ ነገሥታትም ከአንተ ይወጣሉ።

7. በእኔና በአንተ፣ ከአንተም በኋላ ከዘርህ ጋር ከትውልድ እስከ ትውልድ የዘላለም ኪዳኔን እመሠርታለሁ፤ በዚህም የአንተና ከአንተም በኋላ የዘርህ አምላክ (ኤሎሂም) እሆናለሁ።

8. ይህችን አሁን በእንግድነት የምትኖርባትን የከነዓንን ምድር በሙሉ ለአንተና ከአንተም በኋላ ለዘርህ ለዘላለም ርስት አድርጌ እሰጣለሁ፤ አምላካቸውም (ኤሎሂም) እሆናለሁ።”

9. ከዚያም እግዚአብሔር (ኤሎሂም) አብርሃምን እንዲህ አለው፤ “በአንተም በኩል፣ አንተና ከአንተ በኋላ የሚመጣው ዘርህ ከትውልድ እስከ ትውልድ ኪዳኔን ትጠብቃላችሁ።

10. አንተና ከአንተም በኋላ የሚመጣው ዘርህ የምትጠብቁት ኪዳን ይህ ነው፤ በመካከላችሁ ያለ ወንድ ሁሉ ይገረዝ።

11. ስለዚህ ሁላችሁም ሸለፈታችሁን ትገረዛላችሁ፤ ይህም በእኔና በእናንተ መካከል ላለው ኪዳን ምልክት ይሆናል።

12. የሚመጣውም ትውልድ ሁሉ፣ ማንኛውም ወንድ ልጅ፣ ስምንት ቀን ሲሞላው ይገረዝ፤ እንደዚሁም በቤትህ የተወለደውና ከውጭ በገንዘብ የተገዛ ባዕድ ሁሉ ይገረዝ።

13. በቤትህ የተወለደም ሆነ በገንዘብህ የተገዛ ሁሉ መገረዝ አለበት፤ በሥጋችሁ የሚፈጸመው ይህ ኪዳኔ የዘላለም ኪዳን ይሆናል።

14. የሥጋ ሸለፈቱን ያልተገረዘ ማንኛውም ወንድ ኪዳኔን በማፍረሱ ከወገኖቹ ይወገድ።”

15. እግዚአብሔር (ኤሎሂም) አብርሃምን እንዲህ አለው፤ “ሦራን ከእንግዲህ ሦራ ብለህ አትጠራትም፤ ስሟ ከዛሬ ጀምሮ ሣራ ይሁን።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 17