ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 12:7-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

7. እግዚአብሔርም (ያህዌ) ለአብራም ተገልጦ፣ “ይህችን ምድር ለዘርህ እሰጣለሁ” አለው። እርሱም ለተገለጠለት አምላክ (ያህዌ) በዚያ ስፍራ መሠዊያ ሠራ።

8. ከዚያም ተነሥቶ ከቤቴል በስተ ምሥራቅ ወዳሉት ተራሮች ሄደ፤ ቤቴልን በምዕራብ፣ ጋይን በምሥራቅ አድርጎ ድንኳን ተከለ፣ በዚያም ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መሠዊያ ሠራ፤ የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ስም ጠርቶ ጸለየ።

9. አብራምም ከዚያ ተነሥቶ ወደ ኔጌብ ሄደ።

10. በዚያም ምድር ጽኑ ራብ ገብቶ ነበር፤ ከዚህም የተነሣ አብራም ለጥቂት ጊዜ በዚያ ለመኖር ወደ ግብፅ ወረደ።

11. ግብፅ ለመግባት ጥቂት ሲቀረው አብራም ሚስቱን ሦራን እንዲህ አላት፤ “መቼም አንቺ ውብ ሴት መሆንሽን ዐውቃለሁ፤

12. ግብፃውያን አንቺን በሚያዩበት ጊዜ፣ ‘ይህች ሚስቱ ናት’ ብለው እኔን ይገድላሉ፤ አንቺን ግን ይተዉሻል።

13. ስለዚህ ለአንቺ ሲሉ እንዲንከባከቡኝ፣ ሕይወቴም እንድትተርፍ፣ ‘እኅቱ ነኝ’ በዪ።”

14. አብራም በግብፅ አገር እንደ ደረሰ ግብፃውያን፣ ሦራ እጅግ ውብ ሴት እንደሆነች አዩ፤

15. የፈርዖንም ሹማምት ባዩአት ጊዜ፣ ለፈርዖን አድንቀው ነገሩት፤ ወደ ቤተ መንግሥትም ወሰዷት።

16. በእርሷም ምክንያት ፈርዖን አብራምን አክብሮ አስተናገደው፤ በጎችና ከብቶች፣ ተባዕትና እንስት አህዮች፣ ወንድና ሴት አገልጋዮች እንዲሁም ግመሎችን ሰጠው።

17. እግዚአብሔርም (ያህዌ) በአብራም ሚስት በሦራ ምክንያት ፈርዖንንና ቤተ ሰዎቹን በጽኑ ደዌ መታቸው።

18. ከዚያም ፈርዖን አብራምን አስጠርቶ እንዲህ አለው፤ “ይህ ያደረግህብን ነገር ምንድን ነው? ‘ሚስትህ እንደሆነች ለምን አልነገርኸኝም?’

19. ለምን ‘እኅቴ ናት’ አልኸኝ? ሚስቴ ላደርጋት ነበር። በል አሁንም ሚስትህ ይህችው፤ ይዘሃት ሂድ!”

20. ከዚያም ፈርዖን ስለ አብራም ለባለ ሟሎቹ ትእዛዝ ሰጠ፤ እነርሱም አብራምን ከሚስቱና ከንብረቱ ሁሉ ጋር አሰናበቱት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 12