ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 12:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. እግዚአብሔር (ያህዌ) አብራምን እንዲህ አለው፤ “አገርህን፣ ወገንህንና የአባትህን ቤት ትተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ሂድ።

2. “ታላቅ ሕዝብ አደርግሃለሁ፤ደግሞም እባርክሃለሁ፤ስምህን ገናና አደርገዋለሁ፤ለሌሎች በረከት ትሆናለህ።

3. የሚባርኩህን እባርካለሁ፤የሚረግሙህን እረግማለሁ፤በምድር የሚኖሩ ሕዝቦች፣በአንተ አማካይነት ይባረካሉ።”

4. ስለዚህ አብራም እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዳዘዘው ወጣ፤ ሎጥም አብሮት ሄደ። አብራም ከካራን ሲወጣ ዕድሜው 75 ዓመት ነበረ።

5. አብራምም ሚስቱን ሦራንና የወንድሙን ልጅ ሎጥን አስከትሎ በካራን ሳሉ ያፈሩትን ሀብትና የነበራቸውን አገልጋዮች ይዘው በመጓዝ ከነዓን ምድር ገቡ።

6. አብራም ትልቁ የሞሬ ዛፍ እስከሚገኝበት እስከ ሴኬም ድረስ በምድሪቱ ዘልቆ ሄደ። በዚያን ጊዜ ከነዓናውያን በዚሁ ምድር ይኖሩ ነበር።

7. እግዚአብሔርም (ያህዌ) ለአብራም ተገልጦ፣ “ይህችን ምድር ለዘርህ እሰጣለሁ” አለው። እርሱም ለተገለጠለት አምላክ (ያህዌ) በዚያ ስፍራ መሠዊያ ሠራ።

8. ከዚያም ተነሥቶ ከቤቴል በስተ ምሥራቅ ወዳሉት ተራሮች ሄደ፤ ቤቴልን በምዕራብ፣ ጋይን በምሥራቅ አድርጎ ድንኳን ተከለ፣ በዚያም ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መሠዊያ ሠራ፤ የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ስም ጠርቶ ጸለየ።

9. አብራምም ከዚያ ተነሥቶ ወደ ኔጌብ ሄደ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 12