ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፀአት 9:8-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

8. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴንና አሮንን አላቸው፤ “ከምድጃው እፍኝ ዐመድ ወስዳችሁ፣ ሙሴ በፈርዖን ፊት ወደ ሰማይ ይበትነው።

9. በግብፅ ምድር ሁሉ ትቢያ ይሆናል፤ በምድሪቱ ሁሉ በሚገኙት ሰዎችና እንስሳት ላይ መግል የያዘ እባጭ ይወጣል።”

10. ስለዚህ ከምድጃው ዐመድ ወስደው በፈርዖን ፊት ቆሙ፤ ሙሴም ወደ ሰማይ በተነው፤ መግል የያዘ እባጭም በሰዎችና በእንስሳት ላይ ወጣ።

11. በእነርሱና በግብፃውያን ሁሉ ላይ እባጭ ወጥቶ ስለ ነበር፣ አስማተኞቹ በሙሴ ፊት መቆም አልቻሉም።

12. እግዚአብሔር (ያህዌ) ግን የፈርዖንን ልብ አደነደነ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ለሙሴ እንደ ተናገረውም፣ ሙሴንና አሮንን መስማት አልፈለገም።

13. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ማልደህ በጧት ተነሣ፤ ከፈርዖን ፊት ቀርበህ እንዲህ በለው፤ የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር (ያህዌ ኤሎሂም) የሚለው ይህ ነው፤ ያመልኩኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ፤

14. አለዚያ በአንተ በሹማምቶችህና በሕዝብህ ላይ የመቅሠፍቴን መዓት ሁሉ አሁን አወርድብሃለሁ፤ ይኸውም በምድር ሁሉ እንደ እኔ ያለ ማንም እንደሌለ ታውቅ ዘንድ ነው።

15. አሁን እጄን ዘርግቼ አንተንና ሕዝብህን ከገጸ ምድር ሊያጠፋችሁ በሚችል መቅሠፍት በመታኋችሁ ነበር።

16. ነገር ግን ኀይሌን እንዳሳይህና ስሜም በምድር ዙሪያ ሁሉ እንዲታወቅ ለዚህ አስነሥቼሃለሁ።

17. እስካሁንም በሕዝቤ ላይ እንደ ተነሣህ ነው፤ ይሄዱም ዘንድ አትለቃቸውም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፀአት 9