ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፀአት 9:3-13 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

3. የእግዚአብሔር (ያህዌ) እጅ በመስክ ላይ ባሉት እንስሳት፣ በፈረሶችህና በአህዮችህ፣ በግመሎችህና በቀንድ ከብቶችህ፣ በበጎችህና በፍየሎችህ ላይ አስከፊ መቅሠፍት ያመጣብሃል።

4. ነገር ግን እግዚአብሔር (ያህዌ) በእስራኤልና በግብፅ እንስሳት መካከል ልዩነት ያደርጋል፤ ይኸውም የእስራኤል የሆነ ማንኛውም እንስሳ እንዳይሞት ነው።’ ”

5. እግዚአብሔር (ያህዌ) ጊዜን ወስኖ፣ እንዲህ አለ፤ “በነገው ዕለት እግዚአብሔር (ያህዌ) በምድሪቱ ላይ ይህን ያደርጋል።”

6. በማግሥቱም እግዚአብሔር (ያህዌ) ነገሩን ፈጸመው፤ የግብፃውያን እንስሳት በሙሉ አለቁ፤ ነገር ግን የእስራኤላውያን ከሆኑት እንስሳት አንድም አልሞተም።

7. ፈርዖን ያጣሩ ዘንድ ሰዎች ልኮ ከእስራኤላውያኑ እንስሳት አንድም እንኳን አለመሞቱን ተገነዘበ። ያም ሆኖ ልቡ እንደ ደነደነ ስለ ነበር፣ ሕዝቡን አልለቀቀም።

8. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴንና አሮንን አላቸው፤ “ከምድጃው እፍኝ ዐመድ ወስዳችሁ፣ ሙሴ በፈርዖን ፊት ወደ ሰማይ ይበትነው።

9. በግብፅ ምድር ሁሉ ትቢያ ይሆናል፤ በምድሪቱ ሁሉ በሚገኙት ሰዎችና እንስሳት ላይ መግል የያዘ እባጭ ይወጣል።”

10. ስለዚህ ከምድጃው ዐመድ ወስደው በፈርዖን ፊት ቆሙ፤ ሙሴም ወደ ሰማይ በተነው፤ መግል የያዘ እባጭም በሰዎችና በእንስሳት ላይ ወጣ።

11. በእነርሱና በግብፃውያን ሁሉ ላይ እባጭ ወጥቶ ስለ ነበር፣ አስማተኞቹ በሙሴ ፊት መቆም አልቻሉም።

12. እግዚአብሔር (ያህዌ) ግን የፈርዖንን ልብ አደነደነ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ለሙሴ እንደ ተናገረውም፣ ሙሴንና አሮንን መስማት አልፈለገም።

13. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ማልደህ በጧት ተነሣ፤ ከፈርዖን ፊት ቀርበህ እንዲህ በለው፤ የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር (ያህዌ ኤሎሂም) የሚለው ይህ ነው፤ ያመልኩኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፀአት 9