ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፀአት 4:10-23 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

10. ሙሴም እግዚአብሔርን (ያህዌ) ጌታ (አዶናይ) ሆይ፣ ቀድሞም ሆነ፣ አንተ ከባሪያህ ጋር ከተነጋገርህ ወዲህ፣ ከቶ አንደበተ ርቱዕ ሰው አይደለሁም። እኔ ኮልታፋና ንግግር የማልችል ሰው ነኝ” አለው።

11. እግዚአብሔርም (ያህዌ) ሙሴን፣ “ለሰው አንደበቱን የሰጠው ማነው? ሰውን ደንቆሮ ወይም ዲዳ የሚያደርገው ማነው? ዓይን የሚሰጥ ወይም ዕውር የሚያደርገውስ ማነው? እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) አይደለሁምን?”

12. በል አሁን ሂድ፤ እኔ እንድትናገር አደርግሃለሁ፤ የምትናገረውንም አስተምርሃለሁ” አለው።

13. ሙሴ ግን፣ “ጌታ ሆይ (አዶናይ)፤ እባክህ ሌላ ሰው ላክ” አለው።

14. በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ቍጣ በሙሴ ላይ ነደደ፣ “ሌዋዊው ወንድምህ አሮን አለ አይደል? እርሱ ጥሩ እንደሚናገር ዐውቃለሁ፤ እንዲያውም አሁን ወደ አንተ እየመጣ ነው፤ በሚያይህም ጊዜ ከልቡ ደስ ይለዋል።

15. ለእርሱ ትነግረዋለህ፤ የሚናገራቸውንም ቃላት በአንደበቱ ታኖራለህ፤ ሁለታችሁም በትክክል እንድትናገሩ እረዳችኋለሁ፤ ምን ማድረግ እንዳለባችሁም አስተምራችኋለሁ።

16. አንተ እንደ አምላኩ ሆነህ ትነግረዋለህ፤ እርሱም እንደ አንደበትህ ሆኖ ለሕዝቡ ይናገርልሃል።

17. ታምራዊ ምልክት እንድታሳይባት ይህችን በትር በእጅህ ይዘህ ሂድ።”

18. ሙሴም ወደ አማቱ ወደ ዮቶር ተመልሶ ሄደና፣ “ወገኖቼ እስካሁን በሕይወት መኖራቸውን አይ ዘንድ ወደ ግብፅ ተመልሼ እንድሄድ እባክህ ፍቀድልኝ” አለው። ዮቶርም፣ “ሂድ፤ በሰላም ያግባህ” አለው።

19. ሙሴ በምድያም ሳለ እግዚአብሔር (ያህዌ)፣ “አንተን ሊገድሉህ የሚፈልጉ ሰዎች ሁሉ ሞተዋልና ተመልሰህ ወደ ግብፅ ሂድ” አለው።

20. ስለዚህ ሙሴ ሚስቱንና ልጆቹን በአህያ ላይ አስቀምጦ፣ ወደ ግብፅ አገር መመለስ ጀመረ፤ የእግዚአብሔርንም (ኤሎሂም) በትር በእጁ ይዞ ነበር።

21. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፣ “ወደ ግብፅ በምትመለስበት ጊዜ በሰጠሁህ ኀይል የምትሠራቸውን ታምራት ሁሉ በፈርዖን ፊት መፈጸም እንዳለብህ አትዘንጋ። እኔ ግን ሕዝቡን እንዳይለቅ ልቡን አደነድ ነዋለሁ።

22. ስለዚህ ለፈርዖን እንዲህ በለው፤ ‘እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዲህ ይላል፤ እስራኤል የበኵር ልጄ ነው፤

23. “ያመልከኝ ዘንድ ልጄን ልቀቀው” ብዬህ ነበር፤ አንተ ግን እንዳይሄድ ከለከልኸው፤ ስለዚህ የበኵር ልጅህን እገድላለሁ።’ ”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፀአት 4