ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፀአት 39:4-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. ለኤፉዱ ከሁለቱ ጐኖቹ ጋር ተያይዘው ያሉትን የትከሻ ንጣዮችን ሠሩ፤ ይኸውም ማያያዝ እንዲቻል ነው።

5. በጥበብ የተፈተለው መታጠቂያ በተመሳሳይ መልክ ሆኖ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዳዘዘው፣ ከኤፉዱ ጋር አንድ ወጥ የሆነና ከወርቅ፣ ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊና ከቀይ ማግ፣ በቀጭኑ ከተፈተለ ሐር የተሠራ ነበረ።

6. የከበሩ መረግዶችን በወርቅ ፈርጦች በመክፈፍ፣ እንደ ማኅተም የእስራኤልን ልጆች ስሞች ቀረጹባቸው።

7. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዳዘዘው በኤፉዱ የትከሻ ንጣዮች ላይ ለእስራኤል ልጆች እንደ መታሰቢያ ድንጋዮች አያያዟቸው።

8. የደረት ኪሱንም ጥበበኛ ባለ ሙያ እንደሚሠራው ሥራ በተመሳሳይ መንገድ ሠሩት፤ እንደ ኤፉዱም ከወርቅ፣ ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊና ከቀይ ማግ በቀጭኑም ከተፈተለ በፍታ ሠሩት።

9. ርዝመቱ አንድ ስንዝር ወርዱም አንድ ስንዝር ሲሆን፣ ጥንድ ድርብ ሆኖ ባለ አራት ማእዘን ነበረ።

10. ከዚያም የከበሩ ድንጋዮችን በአራት ረድፍ በላዩ ላይ አደረጉበት፤ በመጀመሪያው ረድፍ ሰርድዮን፣ ቶጳዝዮንና የሚያብረቀርቅ ዕንቍ ነበር፤

11. በሁለተኛውም ረድፍ በሉር፣ ሰንፔርና አልማዝ፣

12. በሦስተኛውም ረድፍ ያክንት፣ ኬልቄዶንና አሜቴስጢኖስ፣

13. በአራተኛውም ረድፍ ቢረሌ፣ መረግድና ኢያስጲድ ነበረ፤ በወርቅ ፈርጥ ላይ ተደርገው ነበር።

14. ለእያንዳንዱ የእስራኤል ልጆች ስም አንዳንድ ሆኖ፣ በእያንዳንዱ ላይ እንደ ማኅተም ከዐሥራ ሁለቱ ነገዶች የአንዱ ስም የተቀረጸበት ዐሥራ ሁለት ድንጋዮች ነበሩ።

15. ለደረት ኪሱም ልክ እንደ ገመድ ከንጹሕ ወርቅ የተጐነጐኑ ድሪዎችን አበጁለት።

16. ሁለት የወርቅ ፈርጦችንና ሁለት የወርቅ ቀለበቶችን ሠርተው ቀለበቶቹን ከደረት ኪሱ ሁለት ጐኖች ጋር አያያዟቸው።

17. ሁለቱን የወርቅ ድሪዎች በደረት ኪሱ ጐንና ጐን ካሉት ቀለበቶች ጋር አያያዟቸው፤

18. የድሪዎቹን ሌሎች ጫፎች ከፊት ካለው ከኤፉዱ የትከሻ ንጣዮች ጋር በማገናኘት ከሁለቱ የወርቅ ፈርጦች ጋር አያያዟቸው።

19. ሁለት የወርቅ ቀለበቶችን ሠርተው ከኤፉዱ ቀጥሎ ካሉት ከሌሎቹ ሁለት የደረት ኪስ ጐኖች ጋር ከውስጠኛው ጠርዝ ላይ አያያዟቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፀአት 39