ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፀአት 37:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ባስልኤል ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፣ ወርዱ አንድ ክንድ ተኩል፣ ከፍታው አንድ ክንድ ተኩል የሆነ ታቦት ከግራር ዕንጨት ሠራ።

2. በውስጥና በውጭ በንጹሕ ወርቅ ለበጠው፤ በዙሪያውም የወርቅ ክፈፍ አበጀለት።

3. አራት የወርቅ ቀለበቶችን ሠርቶ ሁለት ቀለበቶችን በአንድ በኩል፣ ሁለት ቀለበቶችንም በሌላ በኩል አድርጎ ከአራቱ እግሮቹ ጋር አያያዛቸው።

4. ከዚያም መሎጊያዎችን ከግራር ዕንጨት ሠርቶ በወርቅ ለበጣቸው።

5. መሎጊያዎቹንም መሸከሚያ እንዲሆኑ በታቦቱ ጐንና ጐን ባሉት ቀለበቶች ውስጥ አስገባቸው።

6. ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፣ ወርዱም አንድ ክንድ ተኩል የሆነ ከንጹሕ ወርቅ የስርየት መክደኛ ሠራ።

7. ከዚያም ከተቀጠቀጠ ወርቅ ሁለት ኪሩቤልን ከመክደኛው ጫፎች ላይ ሠራ።

8. አንዱን ኪሩብ በአንዱ ጫፍ ላይ፣ ሁለተኛውንም ኪሩብ በሌላው ጫፍ ላይ ሠራ፤ ከሁለቱ ጫፎች ላይ ከክዳኑ ጋር አንድ ወጥ አድርጎ ሠራቸው፤

9. ኪሩቤልም የስርየት ክዳኑን በመሸፈን ክንፋቸውን ወደ ላይ ዘርግተው ነበር፤ ኪሩቤል ወደ ስርየት መክደኛው እየተመለከቱ እርስ በርሳቸው ገጽ ለገጽ ነበሩ።

10. ርዝመቱ ሁለት ክንድ፣ ወርዱ አንድ ክንድ፣ ከፍታውም አንድ ክንድ ተኩል የሆነ ጠረጴዛ ከግራር ዕንጨት ሠሩ።

11. ከዚያም በንጹህ ወርቅ በመለበጥ በዙሪያው የወርቅ ክፈፍ አበጁለት።

12. በዙሪያውም ስፋቱ አንድ ስንዝር የሆነ ጠርዝ በማበጀት በጠርዙ ላይ የወርቅ ክፈፍ አደረጉበት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፀአት 37