ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፀአት 34:23-35 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

23. በዓመት ሦስት ጊዜ ወንድ ሁሉ በእስራኤል አምላክ (ኤሎሂም) በልዑል እግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ይቅረብ።

24. አሕዛብን ከፊትህ አስወጣለሁ፤ ድንበርህን አሰፋለሁ፤ በዓመት ሦስት ጊዜ በአምላክህ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ለመቅረብ ስትወጣ፣ ምድርህን ማንም አይመኝም።

25. “እርሾ ካለው ከማንኛውም ነገር ጋር የደም መሥዋዕት ለእኔ አታቅርብ፤ ከፋሲካ በዓል የተረፈው መሥዋዕት እስከ ማለዳ አይቆይ።

26. “የአፈርህን ምርጥ በኵራት ለአምላክህ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ቤት አምጣ። “ጠቦት ፍየልን በእናቱ ወተት አትቀቅል።”

27. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን፣ “እነዚህን ቃሎች ጻፋቸው፤ በእነዚህ ቃሎች መሠረት ከአንተና ከእስራኤል ጋር ቃል ኪዳን አድርጌአለሁና” አለው።

28. ሙሴ እህል ሳይበላ ውሃም ሳይጠጣ ከእግዚአብሔር (ያህዌ) ጋር አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በዚያ ነበር፤ በጽላቶቹ ላይ የቃል ኪዳኑን ቃሎች፣ ዐሥርቱ ትእዛዛትን ጻፈ።

29. ሙሴ ሁለቱን የምስክር ጽላቶች በእጆቹ ይዞ ከሲና ተራራ በወረደ ጊዜ ከእግዚአብሔር (ያህዌ) ጋር ከመነጋገሩ የተነሣ ፊቱ እንደሚያበራ አላወቀም ነበር።

30. አሮንና እስራኤላውያን ሁሉ ሙሴን ባዩት ጊዜ ፊቱ ያበራ ነበር፤ ወደ እርሱ ለመቅረብም ፈርተው ነበር።

31. ሙሴ ግን ጠራቸው፤ ስለዚህ አሮንና የማኅበሩ መሪዎች ወደ እርሱ ተመለሱ፤ እርሱም አናገራቸው።

32. ከዚያም በኋላ እስራኤላውያን ሁሉ ወደ እርሱ ቀረቡ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) በሲና ተራራ የሰጠውን ትእዛዞች ሁሉ ሰጣቸው።

33. ሙሴ ለእነርሱ ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ በፊቱ ላይ መሸፈኛ አደረገ።

34. ከእርሱ ጋር ለመነጋገር ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሀልዎት በሚገባበት ጊዜ ሁሉ ግን፣ እስከሚወጣ ድረስ መሸፈኛውን ያነሣ ነበር፤ በወጣም ጊዜ የታዘዘውን ለእስራኤላውያን ነገራቸው።

35. ፊቱ የሚያበራ መሆኑን አዩ፤ ከዚያም ሙሴ ከእግዚአብሔር (ያህዌ) ጋር ለመነጋገር ተመልሶ እስኪሄድ ድረስ መሸፈኛውን መልሶ በፊቱ ላይ ያደርግ ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፀአት 34