ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፀአት 34:13-24 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

13. መሠዊያዎቻቸውን ሰባብሩ፤ የማምለኪያ ዐምዶቻቸውን አድቅቁ፤ የአሼራ ዐፀዶቻቸውንም ቍረጡ።

14. ስሙ ቀናተኛ የሆነው እግዚአብሔር (ያህዌ) ቀናተኛ አምላክ (ኤሎሂም) ነውና ሌላ አምላክ አታምልክ።

15. “በምድሪቱ ከሚኖሩት ጋር ቃል ኪዳን እንዳታደርግ ተጠንቀቅ፤ ምክንያቱም አምላኮቻቸውን ተከትለው ባመነዘሩና መሥዋዕትም ባቀረቡላቸው ጊዜ ይጋብዙሃል፤ አንተም መሥዋዕታቸውን ትበላለህ።

16. ለወንዶች ልጆችህም ሴቶች ልጆቻቸውን ስታጭላቸውና እነዚህም ሴቶች ልጆች አምላኮቻቸውን በመከተል ሲያመነዝሩ፣ ወንዶች ልጆችህን ተመሳሳይ ድርጊት እንዲፈጽሙ ያነሣሷቸዋል።

17. “ቀልጠው የሚሠሩ አማልክትን አታብጅ።

18. “የቂጣን በዓል አክብር። እንዳዘዝኩህም ለሰባት ቀን እርሾ ያልገባበት ቂጣ ብላ፤ ይህንንም በተወሰነው ጊዜ በአቢብ ወር አድርግ፤ በዚያ ወር ከግብፅ ወጥተሃልና።

19. “የመንጋህ ወይም የበግና የፍየልህ፣ የቀንድ ከብትህ ተባዕት በኵር ሁሉ ሳይቀር፣ ከማሕፀን በኵር ሆኖ የሚወጣ ሁሉ የእኔ ነው።

20. የአህያን በኵር በበግ ጠቦት ዋጀው፤ ካልዋጀኸው ግን አንገቱን ስበረው። በኵር ወንድ ልጆችህን ሁሉ ዋጅ። “ማንም በፊቴ ባዶ እጁን አይቅረብ።

21. “ስድስት ቀን ሥራ፤ በሰባተኛው ቀን ግን ዕረፍ፤ በእርሻና በመከር ወቅት እንኳ ቢሆን ማረፍ አለብህ።

22. “የሰባቱን ሱባዔ በዓል ከስንዴው መከር በኵራቶች ጋር፣ እንዲሁም የመክተቻ በዓልን በዓመቱ መጨረሻ ላይ አክብር።

23. በዓመት ሦስት ጊዜ ወንድ ሁሉ በእስራኤል አምላክ (ኤሎሂም) በልዑል እግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ይቅረብ።

24. አሕዛብን ከፊትህ አስወጣለሁ፤ ድንበርህን አሰፋለሁ፤ በዓመት ሦስት ጊዜ በአምላክህ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ለመቅረብ ስትወጣ፣ ምድርህን ማንም አይመኝም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፀአት 34