ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፀአት 32:6-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. በማግሥቱ ሕዝቡ በማለዳ ተነሥተው የሚቃጠል መሥዋዕት ሠዉ፤ የኅብረት መሥዋዕት አቀረቡ፤ ከዚህም በኋላ ይበሉና ይጠጡ ዘንድ ተቀመጡ፤ ሊዘፍኑም ተነሡ።

7. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን፣ “ከግብፅ ያወጣኻቸው ሕዝብህ ስተዋልና ውረድ አለው፤

8. ካዘዝኋቸው ፈቀቅ ለማለት ፈጣኖች ሆኑ፤ ለራሳቸውም በጥጃ ምስል የተቀረጸ ጣዖትን ሠሩ፤ ለእርሱም ሰገዱለት፤ ሠዉለትም፤ እንዲሁም፣ ‘እስራኤል ሆይ፤ ከግብፅ ምድር ያወጡህ አማልክትህ እነዚህ ናቸው’ ” አሉ።

9. እግዚአብሔርም (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “እነዚህን ሕዝብ አይቻቸዋለሁ፤ አንገተ ደንዳናዎችም ናቸው፤

10. አሁንም በእነርሱ ላይ፣ ቍጣዬ እንዲነድና እንዳጠፋቸው ተወኝ፤ ከዚያም አንተን ለታላቅ ሕዝብ አደርግሃለሁ።”

11. ነገር ግን ሙሴ የአምላኩን የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ቸርነት ፈለገ፤ እንዲህም አለ፤ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ሆይ በታላቅ ሥልጣንህና በኀያል ክንድህ ከግብፅ ባወጣኸው ሕዝብህ ላይ ቍጣህ ለምን ይነዳል?

12. ግብፃውያን፣ ‘በተራራዎቹ ላይ ሊገድላቸው ከገጸ ምድርም ሊያጠፋቸው ስለ ፈለገ ነው ያወጣቸው’ ለምን ይበሉ? ከክፉ ቍጣህ ተመለስ፤ ታገሥ፤ በሕዝብህም ላይ ጥፋት አታምጣ።

13. ለባሪያዎችህ ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለእስራኤል፣ ‘ዘርህን እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛዋለሁ፤ ለዘርህም ተስፋ አድርጌ የሰጠኋቸውን ይህችን ምድር ሁሉ እሰጣቸዋለሁ፤ ለዘላለምም ርስታቸው ትሆናለች’ በማለት በራስህ የማልኸውን አስታውስ።”

14. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ታገሠ፤ በሕዝቡም ላይ አመጣባቸዋለሁ ያለውን ጥፋት አላመጣባቸውም።

15. ሙሴም ሁለቱን የምስክር ጽላቶች በእጆቹ ይዞ ከተራራው ወረደ፤ ጽላቶቹም ከፊትና ከኋላ በሁለቱም ጎኖች ተጽፎባቸው ነበር።

16. ጽላቶቹ የእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ሥራ ነበሩ፤ በጽላቶቹ ላይ የተቀረጸ ጽሕፈትም የእግዚአብሔር (ያህዌ) ጽሕፈት ነበር።

17. ኢያሱ የሕዝቡን የጩኸት ድምፅ በሰማ ጊዜ ሙሴን፣ “በሰፈሩ ውስጥ የጦርነት ድምፅ አለቃ አለው።

18. ሙሴም“የድል ድምፅ አይደለም፤የሽንፈትም ድምፅ አይደለም፤የምሰማው የዘፈን ድምፅ ነው” ብሎ መለሰለት።

19. ሙሴ ወደ ሰፈሩ ደርሶ ጥጃውንና ጭፈራውን ባየ ጊዜ ቍጣው ነደደ፤ ጽላቶቹን ከእጁ በመወርወር ከተራራው ግርጌ ሰባበራቸው።

20. የሠሩትን ጥጃ ወስዶ በእሳት አቃጠለው፤ ከዚያም ዱቄት እስኪሆን ፈጨው፤ በውሃ ላይ በተነው፤ እስራኤላውያንም እንዲጠጡት አደረገ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፀአት 32