ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፀአት 32:12-30 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

12. ግብፃውያን፣ ‘በተራራዎቹ ላይ ሊገድላቸው ከገጸ ምድርም ሊያጠፋቸው ስለ ፈለገ ነው ያወጣቸው’ ለምን ይበሉ? ከክፉ ቍጣህ ተመለስ፤ ታገሥ፤ በሕዝብህም ላይ ጥፋት አታምጣ።

13. ለባሪያዎችህ ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለእስራኤል፣ ‘ዘርህን እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛዋለሁ፤ ለዘርህም ተስፋ አድርጌ የሰጠኋቸውን ይህችን ምድር ሁሉ እሰጣቸዋለሁ፤ ለዘላለምም ርስታቸው ትሆናለች’ በማለት በራስህ የማልኸውን አስታውስ።”

14. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ታገሠ፤ በሕዝቡም ላይ አመጣባቸዋለሁ ያለውን ጥፋት አላመጣባቸውም።

15. ሙሴም ሁለቱን የምስክር ጽላቶች በእጆቹ ይዞ ከተራራው ወረደ፤ ጽላቶቹም ከፊትና ከኋላ በሁለቱም ጎኖች ተጽፎባቸው ነበር።

16. ጽላቶቹ የእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ሥራ ነበሩ፤ በጽላቶቹ ላይ የተቀረጸ ጽሕፈትም የእግዚአብሔር (ያህዌ) ጽሕፈት ነበር።

17. ኢያሱ የሕዝቡን የጩኸት ድምፅ በሰማ ጊዜ ሙሴን፣ “በሰፈሩ ውስጥ የጦርነት ድምፅ አለቃ አለው።

18. ሙሴም“የድል ድምፅ አይደለም፤የሽንፈትም ድምፅ አይደለም፤የምሰማው የዘፈን ድምፅ ነው” ብሎ መለሰለት።

19. ሙሴ ወደ ሰፈሩ ደርሶ ጥጃውንና ጭፈራውን ባየ ጊዜ ቍጣው ነደደ፤ ጽላቶቹን ከእጁ በመወርወር ከተራራው ግርጌ ሰባበራቸው።

20. የሠሩትን ጥጃ ወስዶ በእሳት አቃጠለው፤ ከዚያም ዱቄት እስኪሆን ፈጨው፤ በውሃ ላይ በተነው፤ እስራኤላውያንም እንዲጠጡት አደረገ።

21. አሮንንም፣ “ወደዚህ አስከፊ ኀጢአት ትመራቸው ዘንድ እነዚህ ሕዝብ ምን አደረጉህ?” አለው።

22. አሮንም መልሶ፣ “ጌታዬ ሆይ አትቈጣ ብሎ መለሰለት፤ ይህ ሕዝብ ሁል ጊዜ ለክፋት ያዘነበለ መሆኑን አንተ ታውቃለህ፤

23. እነርሱም ‘በፊታችን የሚሄዱ አማልክት ሥራልን፤ ይህ ከግብፅ ያወጣን ሙሴ ምን እንዳገኘው አናውቅም’ አሉኝ።

24. ስለዚህ፣ ‘ማንኛውም ዐይነት የወርቅ ጌጣጌጥ ያለው ሁሉ ያውልቀው አልኋቸው፤ ከዚያም ወርቁን ሰጡኝ፤ ወደ እሳቱ ጣልሁት፤ ይህም ጥጃ ወጣ።”

25. ሕዝቡ ከቍጥጥር ውጭ እንደሆኑ፣ አሮንም መረን እንደ ለቀቃቸውና በጠላቶቻቸውም ዘንድ መሳለቂያ እንደሆኑ ሙሴ አስተዋለ።

26. ስለዚህ በሰፈሩ መግቢያ ላይ ቆሞ፣ “የእግዚአብሔር (ያህዌ) የሆነ ሁሉ ወደ እኔ ይምጣ” አለ፤ ሌዋውያኑም ሁሉ ከእርሱ ጋር ሆኑ።

27. ከዚያም፣ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር (ያህዌ) የሚለው ይህ ነው፤ ‘እያንዳንዱ ሰው በወገቡ ላይ ሰይፍ ይታጠቅ፤ በሰፈር ውስጥ ከዳር እዳር እየተመላለሰ እያንዳንዱ ወንድሙን፣ ጓደኛውንና ጎረቤቱን ይግደል’ ” አላቸው።

28. ሌዋውያኑ ሙሴ እንዳዘዛቸው ፈጸሙ፤ በዚያኑም ዕለት ከሕዝቡ ሦስት ሺህ ያህል አለቁ።

29. ከዚያም ሙሴ፣ “በራሳችሁ ወንዶች ልጆችና ወንድሞች ላይ በመነሣታችሁ፣ በዛሬዋ ቀን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የተለያችሁ ሆናችኋል፤ በዛሬዋም ዕለት ባርኳችኋል” አለ።

30. በማግሥቱም ሙሴ ሕዝቡን፣ “እጅግ የከፋ ኀጢአት ሠርታችኋል፤ አሁን ግን ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) እወጣለሁ፤ ምናልባት ኀጢአታችሁን ማስተስረይ እችል ይሆናል” አላቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፀአት 32