ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፀአት 31:7-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

7. ይኸውም የመገናኛውን ድንኳን፣ የምስክሩን ታቦት በላዩ ላይ ካለው ከስርየት መክደኛው ጋር፣ ሌሎች የድንኳኑን መገልገያ ዕቃዎች ሁሉ፣

8. ጠረጴዛውን ከነዕቃዎቹ፣ ከንጹሕ ወርቅ የተሠራውን የወርቅ መቅረዝ ከነዕቃዎቹ፣ የዕጣኑን መሠዊያ፣

9. የሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያውን ከነዕቃዎቹ፣ ሰኑን፣ ከነማስቀመጫው፣

10. ከፈትል የተሠሩ ልብሶችን ይኸውም የካህኑን የአሮንን የተቀደሱ ልብሶችንና ካህናት ሆነው ሲያገለግሉ የሚለብሷቸውን የወንድ ልጆቹ ልብሶች፣

11. እንዲሁም የመቅደሱ የሆነውን ቅብዐ ዘይትና ጣፋጭ ሽታ ያለውን ዕጣን እንዲሠሩ ነው፤ ልክ እኔ እንዳዘዝሁህ ያብጇቸው።

12. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

13. “ለእስራኤላውያን ንገራቸው፤ ‘ሰንበቴን ማክበር አለባችሁ፤ ይህም በእኔና በእናንተ መካከል በሚመጡት ትውልዶች ሁሉ ምልክት ይሆናል፤ ይኸውም የምቀድሳችሁ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንደሆንሁ እንድታውቁ ነው።

14. “ለእናንተ ቅዱስ ነውና ሰንበትን አክብሩ፤ ማንም ቢሽረው በሞት ይቀጣል፤ በዚያ ቀን ማንም የሚሠራ ቢኖር ከወገኑ ተነጥሎ ይለይ።

15. ስድስት ቀን ሥራ ይሠራል፤ ሰባተኛው ቀን ግን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የተቀደሰ የዕረፍት ሰንበት ነው፤ በሰንበት ቀን ማንም ቢሠራ በሞት መቀጣት አለበት።

16. እስራኤላውያን በሚመጡት ትውልዶች ሁሉ ሰንበትን በመጠበቅ የዘላለም ኪዳን አድርገው ማክበር አለባቸው፤

17. በእኔና በእስራኤላውያን መካከል ለዘላለም ምልክት ይሆናል፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሰማይንና ምድርን በስድስት ቀን ሠርቶ፣ በሰባተኛው ቀን ከሥራ ታቅቦ ዐርፎአልና።’ ”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፀአት 31