ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፀአት 29:33-46 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

33. ለክህነታቸውና ለመቀደሳቸው ማስተስረያ የሆኑትን እነዚህን መሥዋዕቶችን ይብሉ፤ የተቀደሱ ስለሆኑ ሌላ ማንም አይብላቸው።

34. ከክህነቱ የአውራ በግ ሥጋ ወይም ከቂጣው እስከ ንጋት ድረስ ቢተርፍ አቃጥለው፤ የተቀደሰ ስለ ሆነ መበላት የለበትም።

35. “ክህነታቸውን በሰባት ቀን በመፈጸም ለአሮንና ለወንዶች ልጆቹ ያዘዝሁህን ሁሉ አድርግላቸው።

36. ለማስተስረያ የሚሆን አንድ ወይፈን የኀጢአት መሥዋዕት አድርገህ በየዕለቱ ሠዋ፤ ለመሠዊያውም ማስተስረያ በማቅረብ መሠዊያውን አንጻው፤ ትቀድሰውም ዘንድ ቅባው።

37. ለሰባት ቀን ለመሠዊያው ማስተስረያ በማድረግ ቀድሰው፤ ከዚያም መሠዊያው እጅግ የተቀደሰ ይሆናል፤ የሚነካውም ሁሉ የተቀደሰ ይሆናል።

38. “በየዕለቱ ያለ ማቋረጥ በመሠዊያው ላይ የምታቀርበው ይህ ነው፤ ዓመት የሞላቸው ሁለት የበግ ጠቦቶች፤

39. አንዱን በማለዳ፣ ሌላውን በምሽት አቅርብ።

40. ከመጀመሪያው የበግ ጠቦት ጋር የኢፍ መስፈሪያ አንድ ዐሥረኛ ምርጥ ዱቄትን ተወቅጦ ከተጠለለ ሩብ ኢፍ ዘይት ጋር ለውስና ሩብ ኢን ወይንን ደግሞ የመጠጥ መሥዋዕት በማድረግ አቅርብ።

41. ሌላውን የበግ ጠቦት በማለዳው እንደ ቀረበው ተመሳሳይ ከሆነው የእህልና የመጠጥ መሥዋዕት ጋር በምሽት ሠዋው፤ ይህም ጣፋጭ መዓዛና ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳት የሚቀርብ መሥዋዕት ነው።

42. “ይህ የሚቃጠል መሥዋዕት በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ላይ በሚመጡት ትውልዶች ዘወትር ይደረጋል፤ በዚያ እገናኝሃለሁ፤ እናገርሃለሁም፤

43. በዚያ ደግሞ ከእስራኤላውያን ጋር እገናኛለሁ፤ ስፍራውም በክብሬ ይቀደሳል።

44. “ስለዚህ የመገናኛው ድንኳንና መሠዊያውን እኔ እቀድሳለሁ፤ ካህናት ሆነው እንዲያገለግሉኝ አሮንና ወንድ ልጆቹን እቀድሳለሁ።

45. ከዚያም በእስራኤላውያን መካከል እኖራለሁ፤ አምላካቸውም (ኤሎሂም) እሆናለሁ።

46. በመካከላቸውም እኖር ዘንድ ከግብፅ ያወጣኋቸው እኔ አምላካቸው እግዚአብሔር (ያህዌ) መሆኔን ያውቃሉ፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) አምላካቸው ነኝ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፀአት 29