ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፀአት 29:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. “ካህናት ሆነው እንዲያገለግሉኝ ትቀድሳቸው ዘንድ የምታደርገው ይህ ነው፤ ነውር የሌለባቸው አንድ ወይፈንና ሁለት አውራ በጎች ውሰድ፤

2. እርሾ ከሌለው ከምርጥ የስንዴ ዱቄት ቂጣ፣ በዘይት የተለወሰ የቂጣ እንጎቻና በዘይት የተቀባ ኅብስት ጋግር።

3. በሌማት ላይ አድርገህ ከወይፈኑና ከሁለቱ አውራ በጎች ጋር አቅርባቸው።

4. ከዚያም አሮንና ወንድ ልጆቹን ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ በማምጣት በውሃ እጠባቸው።

5. ልብሶቹን ወስደህ ለአሮን አልብሰው፤ ሸሚዝ፣ የኤፉድ ቀሚስ፣ ኤፉዱንና የደረት ኪሱን አልብሰው፤ ኤፉዱን በእርሱ ላይ በጥበብ በተሠራ መታጠቂያ እሠረው።

6. መጠምጠሚያውን በራሱ ላይ በማድረግ የተቀደሰውን አክሊል ከመጠምጠሚያው ጋር አያይዘው።

7. ቅብዐ ዘይት ወስደህ በራሱ ላይ በማፍሰስ ቅባው።

8. ወንዶች ልጆቹን አምጥተህ ሸሚዞች አልብሳቸው።

9. የራስ ማሰሪያዎችንም አድርግላቸው፤ ከዚያም አሮንንና ወንዶች ልጆቹን መታጠቂያዎችን አስታጥቃቸው፤ ክህነት የዘላለም ሥርዐት ይሆንላቸዋል፤ በዚህም መንገድ አሮንንና ወንዶች ልጆቹን ትክናቸዋለህ።

10. “ወይፈኑን በመገናኛው ድንኳን ፊት ለፊት በማምጣት አሮንና ወንዶች ልጆቹ በራሱ ላይ እጆቻቸውን ይጫኑበት።

11. በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ላይ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት እረደው።

12. ከወይፈኑ ደም ወስደህ በመሠዊያው ቀንዶች ላይ በጣቶችህ አድርግበት፤ የቀረውንም ከመሠዊያው ሥር አፍሰው።

13. ከዚያም በሆድ ዕቃዎች ያለውን ስብ ሁሉ፣ የጉበቱን መሸፈኛና ሁለቱንም ኵላሊቶች በዙሪያቸው ካለው ስብ ጋር ወስደህ በመሠዊያው ላይ አቃጥላቸው።

14. ነገር ግን የወይፈኑን ሥጋ፣ ቆዳውንና የማይበላውን አሰስ ገሠስ ሥጋ ከሰፈር ውጭ አቃጥለው፤ የኀጢአት መሥዋዕት ነው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፀአት 29