ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፀአት 28:24-43 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

24. ሁለቱን የወርቅ ጒንጒኖች በደረት ኪሱ ጐኖች ላይ ካሉት ቀለበቶች ጋር አያይዛቸው።

25. ሌሎቹን የጒንጒን ጫፎች በፊት ላይ ካለው ኤፉድ በትከሻው ላይ ካሉት ንጣዮች ጋር በማጋጠም ከሁለቱ የወርቅ ፈርጦች ጋር አያይዛቸው።

26. ሁለት የወርቅ ቀለበቶች አበጅተህ ከኤፉዱ ቀጥሎ ባለው በውስጠኛ ጠርዝ ላይ፣ በሌላ በኩል ካሉት ሁለት የደረት ኪስ ጒኖች ጋር አያይዛቸው።

27. ሁለት ተጨማሪ የወርቅ ቀለበቶች አበጅተህ ከኤፉዱ መታጠቂያ ከፍ ብሎ ከመጋጠሚያው አጠገብ ካለው በኤፉዱ ፊት ለፊት፣ በትከሻ ላይ ካሉት ንጣዮች ግርጌ ጋር አያይዘው።

28. የደረት ኪሱም ቀለበቶች፣ የደረት ኪሱ ከኤፉዱ ጋር እንዳይላቀቅ፣ ከመታጠቂያው ጋር በማገናኘት በሰማያዊ ገመድ ከኤፉዱ ቀለበቶች ጋር ይያያዙ።

29. “አሮን ወደ መቅደሱ በሚገባበት ጊዜ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ለዘላለም መታሰቢያ ይሆን ዘንድ የእስራኤልን ልጆች ስሞች በፍርድ መስጫው ደረት ኪስ በልቡ ላይ ይሸከም።

30. ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት በሚገባበት ጊዜ በአሮን ልብ ላይ ይሆኑ ዘንድ ኡሪሙንና ቱሚሙን በደረት ኪሱ አድርግ፤ ስለዚህ አሮን ሁል ጊዜ ለእስራኤላውያን የፍርድ መስጫውን በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት በልቡ ላይ ይሸከማል።

31. “የኤፉዱ ቀሚስ ሙሉ በሙሉ ከሰማያዊ ጨርቅ ይሁን፤

32. ከላይ በኩል በመካከሉ ዐንገትጌ አድርገህ አብጀው፤ እንዳይቀደድም በማስገቢያው ዙሪያ እንደ ክሳድ ያለ ዝምዝም ጠርዝ ሥራለት።

33. በጨርቁ ጠርዝ ዙሪያ ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊና ከቀይ ማግ ሮማኖቹን፣ በመካከሉም የወርቅ ሻኵራዎችን አብጅ።

34. የወርቅ ሻኵራዎቹና ሮማኖቹ በጨርቁ ጠርዝ ዙሪያ በመፈራረቅ ይሆናሉ።

35. አሮንም በአገልግሎቱ ጊዜ ይህን መልበስ አለበት፤ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ወደ መቅደሱ በገባና ከመቅደሱ ሲወጣ እንዳይሞት የሻኵራዎቹ ድምፅ ይሰማል።

36. “ከንጹሕ ወርቅ ዝርግ ሳሕን አበጅተህ፣ “ቅዱስ ለእግዚአብሔር (ያህዌ)” በማለት በማኅተም ላይ እንደሚቀረጽ ቅረጸው።

37. ከመጠምጠሚያው ጋር እንዲያያዝ ሰማያዊ ፈትል እሰርበት፤ እርሱም በመጠምጠሚያው ፊት በኩል ይሁን።

38. ይህም በአሮን ግንባር ላይ ይሆናል፤ እስራኤላውያን ለይተው በሚያቀርቧቸው በማናቸውም የተቀደሱ ስጦታዎች ውስጥ ያለውን በደል ይሸከማል፤ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ተቀባይነት እንዲኖራቸው ሁል ጊዜ በአሮን ግንባር ላይ ይሆናል።

39. “ሸሚዙን ከቀጭን በፍታ ሥራ፤ መጠምጠሚያውንም ከቀጭን በፍታ አብጀው፤ መታጠቂያውንም ጥልፍ ጠላፊ የሠራው ይሁን።

40. የአሮን ወንድ ልጆች ክብርና ማዕረግ እንዲኖራቸው ሸሚዞችን፣ መታጠቂያዎችን፣ የራስ ማሰሪያዎችን አብጅላቸው።

41. እነዚህን ልብሶች ለአሮንና ለወንድ ልጆቹ ካለበስህ በኋላ ቅባቸው፤ ካናቸው፤ ካህናት ሆነው ያገለግሉኝም ዘንድ ቀድሳቸው።

42. “ከወገብ ጀምሮ እስከ ጭን የሚደርስ ሰውነትን የሚሸፍን ከበፍታ የተሠራ የውስጥ ቁምጣ አብጅ።

43. አሮንና ወንድ ልጆቹ ወደ መገናኛው ድንኳን በሚገቡበት ጊዜ ወይም በመቅደሱ ለማገልገል ወደ መሠዊያው ሲቀርቡ፣ በደል ፈጽመው እንዳይሞቱ እነዚህን መልበስ አለባቸው። “ለአሮንና ለትውልዶቹ ይህ የዘላለም ሥርዐት ይሆናል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፀአት 28