ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፀአት 26:19-31 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

19. ከሥራቸው የሚሆኑ አርባ የብር መቆሚያዎችን አብጅ፤ በእያንዳንዱ ጒጠት ሥር አንድ መቆሚያ ሲሆን፣ ለእያንዳንዱም ወጋግራ ሁለት መቆሚያዎች ይኑሩ።

20. በሌላው ጎን፣ ከማደሪያው ድንኳን በስተ ሰሜን በኩል ሃያ ወጋግራዎችን አብጅ፤

21. በእያንዳንዱም ወጋግራ ሥር ሁለት ሁለት መቆሚያ ሆኖ አርባ የብር መቆሚያዎችን አብጅ።

22. በዳር በኩል ለሚገኘው ይኸውም በምዕራብ ጠርዝ ላለው የማደሪያው ድንኳን ስድስት ወጋግራዎች አብጅ።

23. ዳርና ዳር ላሉት ማእዘኖች ሁለት ወጋግራዎች አብጅ።

24. በእነዚህ ሁለት ማእዘኖች ላይ ከታች እስከ ላይ ድረስ ድርብ ሲሆኑ በአንድ ቀለበት ውስጥ የሚገጥሙ መሆን አለባቸው፤ በሁለቱም ወገን እንዲሁ መሆን አለበት።

25. ስለዚህ ስምንት ወጋግራዎች አሉ፤ እንዲሁም ዐሥራ ስድስት የብር መቆሚያዎች ሲኖሩ፣ ለእያንዳንዱ ወጋግራ ሁለት ሁለት መቆሚያ ይሆናል።

26. “ደግሞም ከግራር ዕንጨት አግዳሚዎችን አብጅ፤ በአንድ በኩል ላሉት የማደሪያው ድንኳን ወጋግራዎች አምስት፣

27. በሌላው ጎን ላሉት አምስት፣ በማደሪያው ድንኳን ዳር በምዕራብ በኩል ባሉት ወጋግራዎች አምስት አብጅ።

28. መካከለኛው አግዳሚ በወጋግራዎቹ መካከል ከጫፍ እስከ ጫፍ ይተላለፍ።

29. ወጋግራዎቹን በወርቅ ለብጣቸው፤ አግዳሚዎቹን ለመያዝ የወርቅ ቀለበቶች አብጅ፤ አግዳሚዎቹንም በወርቅ ለብጣቸው።

30. “ማደሪያ ድንኳኑንም በተራራው ላይ ባየኸው ዕቅድ መሠረት ትከለው።

31. “ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና በቀጭኑ ከተፈተለ በፍታ መጋረጃ አብጅ፤ እጀ ብልህ ሠራተኛም ኪሩቤልን ይጥለፍበት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፀአት 26