ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፀአት 23:5-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

5. የሚጠላህ ሰው አህያ፣ ጭነት ከብዶት ወድቆ ብታየው ርዳው እንጂ ትተኸው አትሂድ።

6. “በዳኝነት ጊዜ በድኻው ላይ ፍርድ አታጓድልበት።

7. ከሐሰት ክስ ራቅ፤ በደል የሌለበትን ወይም ትክክለኛውን ሰው ለሞት አሳልፈህ አትስጥ፣ በደለኛውን ንጹሕ አላደርግምና።

8. “ጒቦ አትቀበል፤ ጒቦ፣ አጥርተው የሚያዩትን ሰዎች ዐይን ያሳውራል፤ የጻድቃንንም ቃል ያጣምማልና።

9. “መጻተኛውን አትጨቁን፤ በግብፅ መጻተኛ ስለ ነበራችሁ፣ መጻተኛ ምን እንደሚሰማው እናንተ ራሳችሁ ታውቃላችሁና።

10. “ስድስት ዓመት በእርሻህ ላይ ዝራ፤ አዝመራንም ሰብስብ፤

11. ነገር ግን በሰባተኛው ዓመት ምድሪቱን ሳትጠቀምባትና ሳታርሳት እንዲሁ ተዋት፤ ከዚያም በወገንህ መካከል ያሉት ድኾች ከእርሷ ምግብ ያገኛሉ፤ የዱር አራዊትም ከእነርሱ የተረፈውን ይበላሉ። በወይን ቦታህና በወይራ ዛፎችህም ላይ እንዲሁ አድርግ።

12. “ስድስት ቀን ሥራህን ሥራ፤ በሬህና አህያህ በቤትህ የተወለደው ባሪያና መጻተኛው ያርፉ ዘንድ በሰባተኛው ቀን ምንም አትሥራ።

13. ያልኋችሁን ሁሉ ታደርጉ ዘንድ ተጠንቀቁ፤ የሌሎችን አማልክት ስም አትጥሩ፤ ከአፋችሁም አይስሙ።

14. በዓመት ሦስት ጊዜ ለእኔ በዓልን ታከብራላችሁ።

15. “ያልቦካ የቂጣ በዓልን አክብር፤ እንዳዘዝኩህ ሰባት ቀን እርሾ የሌለውን ቂጣ ብላ፤ ይህንንም በአቢብ ወር በተወሰነ ቀን አድርግ፤ በዚያ ወር ከግብፅ ወጥተሃልና።“ማንም በፊቴ ባዶ እጁን አይቅረብ።

16. “በማሳህ ላይ በዘራኸው እህል በኵራት የመከርን በዓል አክብር።“በዓመቱ መጨረሻ በማሳህ ላይ ያለውን እህልህን ስትሰበስብ የመክተቻውን በዓል አክብር።

17. “በዓመት ሦስት ጊዜ ወንድ ሁሉ በጌታ በእግዚአብሔር (አዶናይ ያህዌ) ፊት ይቅረብ።

18. የመሥዋዕትን ደም እርሾ ካለበት ነገር ጋር አድርገህ ለእኔ አታቅርብ።“የበዓል መሥዋዕቴ ስብ እስከ ንጋት ድረስ አይቆይ።

19. “የምድርን ምርጥ ፍሬ በኵራት ለአምላክህ ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) አምጣ።“ጠቦት ፍየልን በእናቱ ወተት አትቀቅል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፀአት 23