ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፀአት 23:10-30 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

10. “ስድስት ዓመት በእርሻህ ላይ ዝራ፤ አዝመራንም ሰብስብ፤

11. ነገር ግን በሰባተኛው ዓመት ምድሪቱን ሳትጠቀምባትና ሳታርሳት እንዲሁ ተዋት፤ ከዚያም በወገንህ መካከል ያሉት ድኾች ከእርሷ ምግብ ያገኛሉ፤ የዱር አራዊትም ከእነርሱ የተረፈውን ይበላሉ። በወይን ቦታህና በወይራ ዛፎችህም ላይ እንዲሁ አድርግ።

12. “ስድስት ቀን ሥራህን ሥራ፤ በሬህና አህያህ በቤትህ የተወለደው ባሪያና መጻተኛው ያርፉ ዘንድ በሰባተኛው ቀን ምንም አትሥራ።

13. ያልኋችሁን ሁሉ ታደርጉ ዘንድ ተጠንቀቁ፤ የሌሎችን አማልክት ስም አትጥሩ፤ ከአፋችሁም አይስሙ።

14. በዓመት ሦስት ጊዜ ለእኔ በዓልን ታከብራላችሁ።

15. “ያልቦካ የቂጣ በዓልን አክብር፤ እንዳዘዝኩህ ሰባት ቀን እርሾ የሌለውን ቂጣ ብላ፤ ይህንንም በአቢብ ወር በተወሰነ ቀን አድርግ፤ በዚያ ወር ከግብፅ ወጥተሃልና።“ማንም በፊቴ ባዶ እጁን አይቅረብ።

16. “በማሳህ ላይ በዘራኸው እህል በኵራት የመከርን በዓል አክብር።“በዓመቱ መጨረሻ በማሳህ ላይ ያለውን እህልህን ስትሰበስብ የመክተቻውን በዓል አክብር።

17. “በዓመት ሦስት ጊዜ ወንድ ሁሉ በጌታ በእግዚአብሔር (አዶናይ ያህዌ) ፊት ይቅረብ።

18. የመሥዋዕትን ደም እርሾ ካለበት ነገር ጋር አድርገህ ለእኔ አታቅርብ።“የበዓል መሥዋዕቴ ስብ እስከ ንጋት ድረስ አይቆይ።

19. “የምድርን ምርጥ ፍሬ በኵራት ለአምላክህ ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) አምጣ።“ጠቦት ፍየልን በእናቱ ወተት አትቀቅል።

20. “እነሆ፤ በጒዞ ላይ ሳለህ የሚጠብቅህንና ወዳዘጋጀሁልህ ስፍራ የሚያስገባህንመልአክ በፊትህ ልኬልሃለሁ።

21. በጥንቃቄ ተከተለው፤ የሚናገረውንም ልብ ብለህ አድምጠው፤ አታምፅበት። ስሜ በርሱ ላይ ነውና ዐመፅህን ይቅር አይልም።

22. የሚናገረውን በጥንቃቄ ብታደምጥና ያልኩህን ሁሉ ብታደርግ ለጠላቶችህ ጠላት እሆናለሁ፤ የሚቃወሙህን እቃወማለሁ።

23. መልአኬ በፊትህ ይሄዳል፤ አንተንም ወደ አሞራውያን፣ ወደ ኬጢያውያን፣ ወደ ፌርዛውያን፣ ወደ ከነዓናውያን፣ ወደ ኤዊያውያንና ኢያቡሳውያን ምድር ያስገባሃል፤ እኔም እነርሱን አጠፋቸዋለሁ።

24. ለአማልክቶቻቸው አትስገድ፤ ወይም አታምልካቸው፤ ወይም ልምዳቸውን አትከተል፤ እነርሱን ማፈራረስ አለብህ፤ የአምልኮ ድንጋዮቻቸውንም ሰባብር።

25. አምላክህን እግዚአብሔርን (ያህዌ) አምልክ፤ በረከቱም በምትበላውና በምትጠጣው ላይ ይሆናል፤ በሽታንም ከአንተ ዘንድ አርቃለሁ።

26. በምድርህም የሚያስወርዳት ወይም መካን ሴት አትኖርም፤ ረጅም ዕድሜም እሰጥሃለሁ።

27. “በሚያጋጥሙህ አሕዛብ ሁሉ ላይ ማስፈራቴን በፊትህ እልካለሁ፤ ግራም አጋባቸዋለሁ፤ ጠላቶችህ ሁሉ ወደ ኋላ ተመልሰው እንዲሸሹ አደርጋለሁ።

28. ኤዊያውያንን፣ ከነዓናውያንን፣ ኬጢያውያንን ከመንገድህ ለማስወጣት ተርብን በፊትህ እሰዳለሁ።

29. ነገር ግን በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ አላወጣቸውም፤ ምክንያቱም ምድሪቱ፣ ባድማ ሆና፣ የዱር አራዊት ይበዙባችኋል።

30. ቍጥርህ ጨምሮ ምድሪቱን ለመውረስ እስክትበቃ ድረስ ጥቂት በጥቂት ከፊታችሁ አባርራቸዋለሁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፀአት 23