ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፀአት 2:13-25 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

13. በማግሥቱም በወጣ ጊዜ ሁለት ዕብራውያን እርስ በርሳቸው ሲጣሉ አየ፤ ጥፋተኛውንም፣ “የገዛ ወገንህን የምትመታው ለምንድን ነው?” አለው።

14. ሰውየውም፣ “አንተን በእኛ ላይ ገዥና ዳኛ ማን አደረገህ? ግብፃዊውን እንደ ገደልኸው እኔንም ልትገድለኝ ትፈልጋለህን?” አለው። ሙሴም፣ “ለካስ ያደረግሁት ነገር ታውቆአል!” በማለት ፈራ።

15. ፈርዖንም ይህን በሰማ ጊዜ፣ ሙሴን ሊገድለው ፈለገ፤ ሙሴ ግን ከፈርዖን ሸሽቶ ወደ ምድያም ሄደ፤ እዚያም እንደ ደረሰ በአንድ የውሃ ጉድጓድ አጠገብ ተቀመጠ።

16. የምድያም ካህን ሰባት ሴቶች ልጆች ነበሩት፤ እነርሱም ወደ ውሃው ጒድጓድ መጥተው የአባታቸውን በጎች ውሃ ለማጠጣት ገንዳውን ሞሉት።

17. እረኞችም መጥተው ሴቶቹን ሲያባርሯቸው ሙሴ ከተቀመጠበት ተነሥቶ ተከላከለላቸው፤ በጎቻቸውንም አጠጣላቸው።

18. ሴቶቹም ወደ አባታቸው ወደ ራጉኤል በተመለሱ ጊዜ፣ “ዛሬስ ያለወትሮአችሁ እንዴት ፈጥናችሁ ተመለሳችሁ?” አላቸው።

19. እነርሱም፣ “አንድ ግብፃዊ ከእረኞች እጅ አዳነን፤ እንዲያውም ውሃ ቀድቶ በጎቻችንን አጠጣልን” አሉት።

20. አባታቸውም፣ “ሴቶች ልጆቹን የት አለ? ለምን ትታችሁት መጣችሁ? ጥሩትና አብሮን እንጀራ ይብላ” አላቸው።

21. ሙሴም ከሰውየው ጋር ለመኖር ተስማማ፤ ራጉኤልም ልጁን ሲፓራን ዳረለት።

22. ሲፓራም ወንድ ልጅ ወለደች፤ ሙሴም፣ “በባዕድ አገር መጻተኛ ነኝ” ሲል የልጁን ስም ጌርሳም ብሎ ጠራው።

23. ከብዙ ዓመት በኋላ፣ የግብፅ ንጉሥ ሞተ፤ እስራኤላውያንም በባርነት ከደረሰባቸው ግፍ የተነሣ ይጮኹ ነበር፤ ከባርነት ቀንበር ለመላቀቅ ያሰሙት ጩኸት ወደ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ደረሰ።

24. እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) የጩኸታቸውን ሲቃ ሰማ፤ ከአብርሃም፣ ከይስሐቅና ከያዕቆብ ጋር የገባውንም ቃል ኪዳን አሰበ።

25. እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) እስራኤላውያንን ተመለከተ፤ ስለ እነርሱም ገደደው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፀአት 2