ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፀአት 18:8-14 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

8. ሙሴም እግዚአብሔር (ያህዌ) ለእስራኤል ሲል በፈርዖንና በግብፃውያን ላይ ያደረገውን ሁሉ፣ በመንገድም ላይ ስላጋጠማቸው መከራ ሁሉና እግዚአብሔርም (ያህዌ) እንዴት እንዳዳናቸው ለአማቱ ነገረው።

9. ዮቶርም እግዚአብሔር (ያህዌ) እነርሱን ከግብፃውያን እጅ በመታደግ ለእስራኤል ያደረገውን በጎ ነገር ሁሉ በመስማቱ ተደሰተ።

10. እንዲህም አለ፤ “ከግብፃውያን እጅና ከፈርዖን ለታደጋችሁ፣ ከግብፃውያን እጅ ሕዝቡን ለታደገ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ምስጋና ይሁን”።

11. “እግዚአብሔር (ያህዌ) ከአማልክት ሁሉ በላይ ኀያል እንደሆነ አሁን ዐወቅሁ፤ እስራኤልን በትዕቢት ይዘው በነበሩት ሁሉ ላይ ይህን አድርጎአልና።”

12. ከዚያም የሙሴ አማት ዮቶር የሚቃጠል መሥዋዕትና ሌሎች መሥዋዕቶች ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም) አቀረበ፤ አሮንም ከሙሴ አማት ጋር በእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ፊት እንጀራ ለመብላት ከእስራኤል አለቆች ሁሉ ጋር መጣ።

13. በማግሥቱ ሙሴ ሕዝቡን ለመዳኘት ተቀመጠ፤ እነርሱም በዙሪያው ከጧት እስከ ማታ ድረስ ቆሙ።

14. አማቱም ሙሴ ለሕዝቡ የሚያደርገውን ሁሉ ባየ ጊዜ፣ “ምን ማድረግህ ነው? እነዚህ ሁሉ ሰዎች ከጧት እስከ ማታ በዙሪያህ ቆመው ሳለ፣ ብቻህን በፍርድ ወንበር ላይ ለምን ትቀመጣለህ?” አለው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፀአት 18