ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፀአት 12:27-37 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

27. ‘ግብፃውያንን በቀሠፈ ጊዜ፣ በግብፅ ምድር የእስራኤላውያንን ቤት አልፎ በመሄድ ቤታችንን ላተረፈ፣ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የፋሲካ መሥዋዕት ነው’ ብላችሁ ንገሯቸው።” ከዚያም ሕዝቡ አጐነበሱ፤ ሰገዱም።

28. እስራኤላውያንም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴንና አሮንን እንዳዘዛቸው አደረጉ።

29. እኩለ ሌሊት ላይ እግዚአብሔር (ያህዌ) በግብፅ ምድር በዙፋን ላይ ከተቀመጠው ከፈርዖን የበኵር ልጅ ጀምሮ በጨለማ እስር ቤት ውስጥ እስካለው እስረኛ የበኵር ልጅ ድረስ ያለውንና የእንስሳቱን በኵሮች ሁሉ ቀሠፋቸው።

30. ፈርዖን፣ ሹማምቱና የግብፅ ሕዝብ በሙሉ ሌሊቱን ከመኝታቸው ተነሡ፤ እነሆ በመላይቱ ግብፅ ለቅሶና ዋይታ ነበር፤ ሰው ያልሞተበት አንድም ቤት አልነበረምና።

31. ፈርዖን ሙሴንና አሮንን ሌሊቱን አስጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “ተነሡ እናንተና እስራኤላውያን ከሕዝቤ መካከል ውጡ ሂዱ፤ በጠየቃችሁት መሠረት እግዚአብሔርን (ያህዌ) አምልኩ፤

32. እንዳላችሁት የበግና የፍየል መንጋችሁን፣ የቀንድና የጋማ ከብቶቻችሁን ይዛችሁ ሂዱ፤ እኔንም ባርኩኝ።”

33. ግብፃውያን አገራቸውን በአስቸኳይ ለቀው እንዲወጡላቸው እስራኤላውያንን አጣደፏቸው። “አለበለዚያማ ሁላችንም ማለቃችን ነው” አሉ።

34. ስለዚህ ሕዝቡ ያልቦካውን ሊጥ በየቡሆ ዕቃው አድርገው በጨርቅ ጠቅልለው በትከሻቸው ተሸከሙ።

35. እስራኤላውያን ሙሴ እንዳዘዛቸው የብርና የወርቅ ዕቃዎች እንደዚሁም ልብስ እንዲሰጧቸው ግብፃውያኑን ጠየቋቸው።

36. እግዚአብሔር (ያህዌ) በግብፃውያን ፊት ለእስራኤላውያን ሞገስ ስለሰጣቸው፣ የጠየቋቸውን ሁሉ ሰጧቸው፤ ስለዚህ የግብፃውያንን ንብረት በዝብዘው ወሰዱ።

37. እስራኤላውያን ከራምሴ ተነሥተው ወደ ሱኮት ሄዱ፤ ከሴቶቹና ከልጆቹ ሌላ፣ ስድስት መቶ ሺህ እግረኛ ወንዶች ነበሩ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፀአት 12