ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፀአት 12:20-32 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

20. እርሾ ያለበትን ምንም ነገር አትብሉ፤ በምትኖሩበት ስፍራ ሁሉ ያልቦካ ቂጣ ነዉ መብላት ያለባችሁ።

21. ከዚያም ሙሴ የእስራኤልን ሕዝብ አለቆች በሙሉ አስጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “ቶሎ ሄዳችሁ ለየቤተ ሰቦቻችሁ የሚሆን ጠቦት መርጣችሁ የፋሲካን በግ እረዱ።

22. ከዚያም ጭብጥ የሂሶጵ ቅጠል በመውሰድ፣ በሳህን ውስጥ ካለው ደም ነክራችሁ የየቤቶቻችሁን ጉበንና ግራ ቀኝ መቃኑን ቀቡ። ከእናንተ አንድም ሰው እስኪነጋ ድረስ ከቤቱ አይውጣ።

23. እግዚአብሔር (ያህዌ) ግብፃውያንን ለመቅሠፍ በምድሪቱ ላይ በሚያልፍበት ጊዜ በጉበኑና በመቃኑ ላይ ያለውን ደም ሲያይ ያንን ደጃፍ አልፎ ይሄዳል፤ ቀሣፊውም ወደ ቤታችሁ ገብቶ እንዳይገድላችሁ ይከለክለዋል።

24. “እናንተም ሆነ ልጆቻችሁ ይህን መመሪያ ቋሚ ሥርዐት አድርጋችሁ ትታዘዛላችሁ።

25. እግዚአብሔር (ያህዌ) እሰጣችኋለሁ ብሎ በገባው ቃል መሠረት ወደ ምድሪቱ ስትገቡ ይህን ሥርዐት ጠብቁ።

26. ልጆቻችሁ ስለ ሥርዐቱ ምንነት ሲጠይቋችሁ፣

27. ‘ግብፃውያንን በቀሠፈ ጊዜ፣ በግብፅ ምድር የእስራኤላውያንን ቤት አልፎ በመሄድ ቤታችንን ላተረፈ፣ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የፋሲካ መሥዋዕት ነው’ ብላችሁ ንገሯቸው።” ከዚያም ሕዝቡ አጐነበሱ፤ ሰገዱም።

28. እስራኤላውያንም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴንና አሮንን እንዳዘዛቸው አደረጉ።

29. እኩለ ሌሊት ላይ እግዚአብሔር (ያህዌ) በግብፅ ምድር በዙፋን ላይ ከተቀመጠው ከፈርዖን የበኵር ልጅ ጀምሮ በጨለማ እስር ቤት ውስጥ እስካለው እስረኛ የበኵር ልጅ ድረስ ያለውንና የእንስሳቱን በኵሮች ሁሉ ቀሠፋቸው።

30. ፈርዖን፣ ሹማምቱና የግብፅ ሕዝብ በሙሉ ሌሊቱን ከመኝታቸው ተነሡ፤ እነሆ በመላይቱ ግብፅ ለቅሶና ዋይታ ነበር፤ ሰው ያልሞተበት አንድም ቤት አልነበረምና።

31. ፈርዖን ሙሴንና አሮንን ሌሊቱን አስጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “ተነሡ እናንተና እስራኤላውያን ከሕዝቤ መካከል ውጡ ሂዱ፤ በጠየቃችሁት መሠረት እግዚአብሔርን (ያህዌ) አምልኩ፤

32. እንዳላችሁት የበግና የፍየል መንጋችሁን፣ የቀንድና የጋማ ከብቶቻችሁን ይዛችሁ ሂዱ፤ እኔንም ባርኩኝ።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፀአት 12