ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፀአት 1:9-22 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

9. እርሱም ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፤ “እነሆ፤ እስራኤላውያን በቍጥር በልጠውናል፤ ከእኛም ይልቅ እየበረቱ ነው፤

10. ቍጥራቸው እንዳይጨምር፣ ጦርነት ቢነሣ ከጠላቶቻችን ጋር አብረው እንዳይወጉንና ከምድሪቱም ኮብልለው እንዳይሄዱ ዘዴ እንፈልግ።”

11. ስለዚህ እያስጨነቁ የግዳጅ ሥራ የሚያሠሯቸውን አሠሪ አለቆች ሾሙባቸው። እስራኤላውያንም ፊቶምና ራምሴ የተባሉ ንብረት ማከማቻ ከተሞችን ለፈርዖን ሠሩለት።

12. ነገር ግን ባስጨነቋቸው መጠን የእስራኤላውያን ቍጥር በዛ፤ በምድሪቱም እየተስፋፉ ሄዱ፤ ከዚህም የተነሣ ግብፃውያኑ እስራኤላውያንን እጅግ ፈሯቸው፤

13. ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታም ያሠሯቸው ጀመር።

14. ጭቃ በማስቦካት፣ ጡብ በማሠራትና በእርሻም ሁሉ እያስጨነቁ ከባድ ሥራ እንዲሠሩ በማድረግ ሕይወታቸውን አስመረሩ፤ ግብፃውያኑ በሚያሠሯቸው ከባድ ሥራ ሁሉ ፈጽሞ አይራሩላቸውም ነበር።

15. የግብፅም ንጉሥ ሲፓራና ፉሐ የተባሉትን ዕብራውያን ሴቶች አዋላጆች እንዲህ አላቸው፤

16. “የዕብራውያንን ሴቶች በማማጫው ድንጋይ ላይ በምታዋልዱበት ጊዜ የሚወለደው ሕፃን ወንድ ከሆነ ግደሉት፤ ሴት ከሆነች ግን በሕይወት ትኑር።”

17. አዋላጆቹ ግን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም) ስለ ፈሩ የግብፅ ንጉሥ ያዘዛቸውን አልፈጸሙም፤ ወንዶቹንም ልጆች በሕይወት እንዲኖሩ ተዉአቸው።

18. ንጉሡም አዋላጆቹን ጠርቶ፣ “ለምንድን ነው ወንዶቹን ልጆች በሕይወት እንዲኖሩ የተዋችኋቸው?” አላቸው።

19. እነርሱም፣ “የዕብራውያን ሴቶች እንደ ግብፃውያን ሴቶች አይደሉም፤ ብርቱዎች ስለሆኑ አዋላጆች ከመድረሳቸው በፊት ይወልዳሉ” ሲሉ ለፈርዖን መለሱለት።

20. ከዚህም የተነሣ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ለአዋላጆቹ መልካም ሆነላቸው፤ ሕዝቡም በቍጥር እየበዛና እያየለ ሄደ።

21. አዋላጆቹም እግዚአብሔርን (ኤሎሂም) በመፍራታቸው ቤተ ሰብ ሰጣቸው።

22. ፈርዖንም፣ “የሚወለደውን ወንድ ልጅ ሁሉ አባይ ወንዝ ውስጥ ጣሉት፤ ሴት ልጅ ሁሉ ግን በሕይወት ትኑር” ሲል ሕዝቡን አዘዘ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፀአት 1