ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘዳግም 9:21-29 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

21. ደግሞም ያን የኀጢአት ሥራችሁን፣ አበጅታችሁት የነበረውን ጥጃ ወስጄ፣ በእሳት አቃጠልሁት፤ ከዚያም ሰባብሬ እንደ ትቢያ ዱቄት እስኪሆን ድረስ ፈጭቼ ከተራራው በሚወርደው ጅረት ውስጥ በተንሁት።

22. በተቤራም፣ በማሳህና በቂብሮት ሐታአዋ እግዚአብሔርን (ያህዌ) አስቈጣችሁት።

23. እግዚአብሔር (ያህዌ) ከቃዴስ በርኔ ባስ ወጣችሁ ጊዜ፣ “ውጡ፤ የሰጠኋችሁንም ምድር ርስት አድርጋችሁ ውረሷት” አላችሁ። እናንተ ግን በአምላካችሁ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ትእዛዝ ላይ ዐመፃችሁ፤ እርሱን አልታመናችሁበትም፤ አልታዘዛችሁትምም።

24. እኔ እናንተን ካወቅኋችሁ ጊዜ ጀምሮ፣ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ላይ እንዳመፃችሁ ናችሁ።

25. እግዚአብሔር (ያህዌ) እናንተን እንደሚያ ጠፋችሁ ተናግሮ ስለ ነበር፣ በእነዚያ አርባ ቀናትና አርባ ሌሊቶች በእግዚአብሔር ፊት በግንባሬ ተደፋሁ፤

26. እንዲህም በማለት ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጸለይሁ፤ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ (አዶናይ ያህዌ) በታላቅ ኀይልህ የተቤዠኸውንና በኀያል ክንድህ ከግብፅ ያወጣኸውን፣ ያንተ ርስት የሆነውን ሕዝብህን አታጥፋ።

27. ባሪያዎችህን አብርሃምን፣ ይስሐቅንና ያዕቆብን አስብ፤ የዚህን ሕዝብ ልበ ደንዳናነት፣ ክፋትና ኀጢአት አትመልከት።

28. አለበለዚያ እኛን ካመጣህበት ምድር ያሉ ሰዎች “እግዚአብሔር (ያህዌ) ተስፋ ወደ ሰጣቸው ምድር ሊያገባቸው ስላልቻለና ስለጠላቸው፤ ‘በምድረ በዳ ሊገድላቸው አወጣቸው ይላሉ።’

29. ነገር ግን እነርሱ በታላቅ ኀይልህና በተዘረጋች ክንድህ ያወጣሃቸው ሕዝብህና ርስትህ ናቸው።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘዳግም 9