ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘዳግም 9:14-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

14. አጠፋቸውና ስማቸውንም ከሰማይ በታች እደመስሰው ዘንድ ተወኝ፤ አንተንም ከእነርሱ ይልቅ ብርቱና ብዙ ሕዝብ አደርግሃለሁ።”

15. ስለዚህ ተራራው በእሳት እየተቀጣጠለ ሳለ፣ ሁለቱን የቃል ኪዳን ጽላቶች በሁለቱም እጆቼ እንደያዝሁ ከተራራው ተመልሼ ወረድሁ።

16. በእርግጥ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ላይ ኀጢአት ሠርታችሁ እንደ ነበር ተመለከትሁ፤ ቀልጦ የተሠራ የጥጃ ምስልም ለራሳችሁ አበጃችሁ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) እናንተን ካዘዛችሁ መንገድ በፍጥነት ወጥታችሁ ነበር።

17. ስለዚህ ሁለቱን ጽላቶች ወስጄ ከእጆቼ አሽቀንጥሬ በፊታችሁ ሰባ በርኋቸው።

18. ከዚያም በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ክፉ ነገርን በመፈጸም ለቊጣ እንዲነሣሣ የሚያደርገውን ኀጢአት ሁሉ ስለ ሠራችሁ፣ እህል ውሃ ሳልቀምስ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት እንደ ገና በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት በግምባሬ ተደፋሁ።

19. እናንተን ሊያጠፋችሁ ክፉኛ ተቈጥቶ ነበርና፣ እኔም የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ቊጣና መዓት ፈራሁ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ግን እንደ ገና ሰማኝ።

20. እግዚአብሔር (ያህዌ) አሮንን ሊያጠፋው ክፉኛ ተቈጥቶ ነበር፤ በዚያን ጊዜ ለአሮንም ጸለይሁ።

21. ደግሞም ያን የኀጢአት ሥራችሁን፣ አበጅታችሁት የነበረውን ጥጃ ወስጄ፣ በእሳት አቃጠልሁት፤ ከዚያም ሰባብሬ እንደ ትቢያ ዱቄት እስኪሆን ድረስ ፈጭቼ ከተራራው በሚወርደው ጅረት ውስጥ በተንሁት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘዳግም 9